Search

ለ7ኛ ጠቅላላ ምርጫ የተመዘገቡት ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጮች እነማን ናቸው?

ቅዳሜ ግንቦት 22, 2018 30

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተከናወነውን የመራጮች ምዝገባ ዝርዝር መረጃ ይፋ ያደረገ አድርጓል።

በጥቅሉ 54 ሚሊዮን 57 ሺህ 861 መራጮች መመዝገባቸውን የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ገልጸዋል።

ይህ ሰፊ ቁጥር እነማንን ያካተተ እንደሆነ እና በምን ዓይነት ሁኔታ እንደተመዘገቡ ቦርዱ በዝርዝር አብራርቷል።

ምርጫ ቦርድ በመጀመሪያው ዙር ይፋ ካደረገው አጠቃላይ 50.5 ሚሊዮን ተመዝጋቢዎች መካከል አብዛኛውን ቁጥር የያዙት ሴቶች ናቸው። ቁጥራቸውም 27 ሚሊዮን 390 ሺህ 729 ደርሷል፤ ወንዶች ደግሞ 23 ሚሊዮን 123 ሺህ 426 ሆነው ተመዝግበዋል።

በዚሁ የመጀመሪያ ዙር ይፋ ከተደረጉት መካከል በምዝገባ ዘዴ ረገድ ሲታይ፣ 45 ሚሊዮን 10 ሺህ 594 መራጮች በማኑዋል የተመዘገቡ ናቸው፤ ቀሪዎቹ 5 ሚሊዮን 503 ሺህ 561 መራጮች ደግሞ ዘመናዊውን የዲጂታል ዘዴ ተጠቅመው የተመዘገቡ መሆናቸውን ቦርዱ አመልክቷል።

በፀጥታ ስጋት ምክንያት በመደበኛው ጊዜ ሳይመዘገቡ ቆይተው በኋላ ላይ ቦርዱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመምከር ባመቻቸው ልዩ የጊዜ ሰሌዳ 40 የምርጫ ክልሎች የተመዘገቡ 3 ሚሊዮን 368 ሺህ 454 መራጮችም የዚህ አጠቃላይ ቁጥር አካል ናቸው።

ከዚህ ባለፈም ቦርዱ ባደራጃቸው ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች አማካኝነት 20 ሺህ 122 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በዲጂታል ሲስተም የተመዘገቡ መሆናቸውን ሰብሳቢዋ ጠቅሰዋል።

28 ሺህ 632 የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና 126 ሺህ 498 የወታደራዊ ካምፕ አባላትም ተካትተው ምዝገባው መጠናቀቁ ተገልጿል።

በለሚ ታደሰ