Search

በዜጎች ላይ የ1.7 ቢሊዮን ብር ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩት የፊንቴክ ኢንቨስትመንት ድርጅት መስራችና ባለቤቶች ላይ ምርመራ ተጠናቆ ክስ መመሥረቱን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ

ቅዳሜ መጋቢት 19, 2018 1138

የፊንቴክ ኢንቨስትመንት የግል ድርጅት መስራችና ባለቤቶች የሆኑት ዳንኤል ዮሃንስ ኢየሱስ እና ግርማይ ገብረሚካኤል ይህደጎ የተባሉ ተጠርጣሪዎች፣ ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን በመጠቀም ከ1,200 በላይ ዜጎችን በማጭበርበር የ1.7 ቢሊዮን ብር ጉዳት በማድረሳቸው ፖሊስ በ19 ዓይነት የተለያዩ ወንጀሎች ምርመራውን አጣርቶ ለዓቃቤ ሕግ በመላክ ክስ እንዲመሰረትባቸው ማድረጉን ገልጿል።
 
መጀመሪያ ላይ ክሱ የቀረበው ለአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የነበረ ቢሆንም፣ ወንጀሉ ውስብስብ፣ ከፍተኛ ልምድ የሚጠይቅና ድንበር ተሻጋሪ በመሆኑ ምርመራው በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በኩል በሰፊው ሲጣራ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት ተጠርጣሪ ዳንኤል ዮሃንስ ክስ ተመስርቶበት በማረሚያ ቤት ሆኖ ጉዳዩን እንዲከታተል የተደረገ ሲሆን፣ ሌላኛው ተጠርጣሪ ግርማይ ገብረሚካኤልን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ክትትል እየተደረገ ይገኛል።
 
ግርማይ ገብረሚካኤል በአውሮፓውያኑ 2010 የደቡብ አፍሪካ ዓለም ዋንጫ ወቅትም "አስካሉካን" በተባለ ድርጅት ስም ዜጎችን በማጭበርበር በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ይዞ ከሀገር ቢሰወርም፣ በወቅቱ በኢንተርፖል አማካኝነት ተይዞ ለሕግ መቅረቡን የወንጀል ሪከርዱ ያመላክታል።
 
ተጠርጣሪዎቹ ተጎጂዎችን በ90 ቀናት ውስጥ የመኪና ባለቤት እናደርጋችኋለን በማለት የ950 ሺህ ብር (50%) ቅድመ ክፍያ እንዲፈጽሙና ቀሪውን ገንዘብ ያለወለድ በ5 ዓመት በባንክ ብድር እንደሚጨርሱ በማሳመን ነው ወንጀሉን የፈጸሙት።
ሕዝብን ለማሳመን ሲሉ 148 መኪኖችን ከጅቡቲ በማስገባት 100ዎቹን ለተወሰኑ ሰዎች ማከፋፈላቸውንና ቀሪዎቹን 48 ዘመናዊ መኪኖች በድብቅ መሸጣቸውን ፖሊስ አረጋግጧል።
 
በተጨማሪም 350 መኪኖች ወደ ሀገር መግባታቸውንና 400 መኪኖች ጅቡቲ ወደብ መድረሳቸውን የሚገልጽ የሐሰት መረጃ ለተጎጂዎች ሲሰጡ እንደነበር በምርመራው ተደርሶበታል።
ተጠርጣሪዎቹ የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ከሆነው የቻይናው BYD ካምፓኒ ጋር ምንም ዓይነት ውል ሳይኖራቸው ውል እንዳላቸው በማስመስልና በመስቀል አደባባይ ከተለያዩ ቦታዎች በትውስት ያሰባሰቧቸውን መኪኖች ድርጅቱ ያስገባቸው በማስመሰል የማጭበርበር ወንጀል ሲፈጽሙ ቆይተዋል።
 
በጅቡቲ "አልፋቲዞ" የተባለ ድርጅት በማቋቋም መኪኖቹን በ10% ቅድመ ክፍያ ተረክበው፣ ቀሪውን 90% ክፍያ ሳይፈጽሙ ጅቡቲ ላይ መልሰው መሸጣቸውም በምርመራው ተረጋግጧል።
ፖሊስ እንዳረጋገጠው ተጠርጣሪዎቹ ከእያንዳንዱ ተጎጂ ለቅድመ ክፍያ፣ ለመንግሥት ታክስና ለቻርጀር ማሰሪያ በሚል በአጠቃላይ 1 ሚሊዮን 365 ሺህ ብር ተቀብለዋል።
 
የፊንቴክ ኢንቨስትመንት ድርጅትን ባልተገባና በተጋነነ መልኩ በማስተዋወቅ፣ በሕገወጥ መንገድ ከተሰበሰበው ገንዘብ ተጋሪ በመሆን የተጠረጠሩት አርቲስቶችና የማስታወቂያ ባለሙያዎች ሰለሞን ቦጋለ፣ ሰራዊት ፍቅሬ፣ ዳንኤል ተገኝ፣ አብርሃም ግዛው፣ ይገረም ደጀኔ፣ መንሱር ጀማል እና ካሊድ ናስር በቁጥጥር ሥር ውለው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
 
ፍርድ ቤቱም በእነዚህ ግለሰቦች ላይ እስከ መጋቢት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል። እነዚህ ግለሰቦች ዕውቅናቸውን በመጠቀም የሐሰት መረጃዎችን በማሰራጨትና እያንዳንዳቸው 8 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የ"BYD Song Plus" መኪና በስጦታ በመቀበል ወንጀሉን በማሳለጥ ተጠርጥረዋል።
 
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በማጭበርበር፣ በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ (Money laundering) እና በድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ የጀመረውን ምርመራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
 

 

ይህ ውስብስብ ወንጀል ተጣርቶ ክስ እንዲመሰረት ከፖሊስ ጋር በትብብር ለሠራው የፍትሕ ሚኒስቴር እና መረጃ ሲሰጥ ለነበረው ማኅበረሰብ ፖሊስ ላቅ ያለ ምስጋና ማቅረቡን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለኢቢሲ በላከው መግለጫ አስታውቋል።