Search

ከውጭ ምርት ጥገኝነት ወደ ሀገር በቀል የኢንዱስትሪ ሉዓላዊነት፡ የኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ የሽግግር ጉዞ

እሑድ መጋቢት 20, 2018 225

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በቅርቡ ከቃና ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ ከውጭ ምርት ጥገኝነት ወደ ሀገር በቀል የኢንዱስትሪ ሉዓላዊነት የምታደርገውን ስትራቴጂያዊ ሽግግር በዝርዝር አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም ብረት፣ ግራናይት፣ እብነበረድ፣ ሴራሚክ እና መስታወት በሀገር ውስጥ በበቂ ሁኔታ ባለመመረታቸው በግንባታው ዘርፍ ላይ እያሳደሩት ያለውን ተፅዕኖ ገልጸዋል።

የመሰረተ ልማት እና የኃይል አቅርቦት ችግሮችን በመፍታት ወደ ተግባር በመገባቱ ኢንዱስትሪው አዎንታዊ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዘርፉ በሚቀጥሉት ሦስት እና አራት ዓመታት ውስጥ አስተማማኝ ቁመና ላይ እንደሚደርስ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ከስድስት ወራት በኋላ የሴራሚክ ምርትን፣ ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ የመስታወት ምርትን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ በመተካት ከውጭ ማስገባት እንደምታቆም የተገለጸ ሲሆን፣ እብነበረድ እና ግራናይትንም በቅርብ ጊዜ ውስጥ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ታቅዷል።

የኢንዱስትሪው ዋነኛ የጀርባ አጥንት የሆነውን የብረት ምርትም በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችሉ ፈቃዶች መሰጠታቸውን ጠቅሰው፣ ይህም ለግንባታ ግብዓቶች የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት ኢትዮጵያን የብረት ምርት ላኪ እስከማድረግ የሚያደርስ ራዕይ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ስትራቴጂያዊ እርምጃ በመደመር መንግሥት የኢኮኖሚ ዕድገት እሳቤ ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ ብሔራዊ ሀብትን፣ የከተማ ልማት ፍላጎትንና የኢንዱስትሪ አቅምን በማቀናጀት የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ታልሞ እየተሠራ ነው።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በተናጠል እየተገነቡ ያሉት ዘመናዊ እና ግዙፍ ፋብሪካዎች ለሴራሚክ እና ለመስታወት ምርት የተቀመጠውን የጊዜ ገደብ ተጨባጭ ያደርጉታል።

እነዚህን የኢንዱስትሪ ግብዓቶች በሀገር ውስጥ ማምረት ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ እና የሀገራችንን የክፍያ ሚዛን ለማረጋጋት እንደ ዋነኛ ማክሮ ኢኮኖሚያዊ መፍትሔ ይወሰዳል።

በተለይም የብረት ኢንዱስትሪ በኢኮኖሚው ውስጥ ሰፊ የሆነ የኋሊት እና የፊት ትስስር ያለው በመሆኑ፣ በዘርፉ የሚፈጠር እያንዳንዱ የአንድ ዶላር ተጨማሪ እሴት በሌሎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ላይ 2.5 እጥፍ ዕድገት እንደሚያስከትል ጥናቶች ያሳያሉ።

በግንባታው ዘርፍ የሀገር ውስጥ ምርቶች መኖራቸው የግብዓት ዋጋ መዋዠቅን በመቀነስ፣ በዓለም አቀፍ ገበያ አለመረጋጋት እና በሎጂስቲክስ መጓተት ምክንያት የሚከሰተውን ከፍተኛ የፕሮጀክት በጀት ጭማሪ ያስቀራል።

ይህም እንደ ኮሪደር ልማት እና ሰፊ የቤት ግንባታ ያሉ ብሔራዊ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እና ወጪ እንዲከናወኑ ዕድል ይፈጥራል።

ከመስታወት ምርት ጋር ተያይዞም የኢኒሼቲቩ መሳካት ከግንባታ ግብዓት ባለፈ ለመጠጥ እና ለመድኃኒት ኢንዱስትሪዎች፣ በተለይም ለክትባት ማምረቻ የሚሆኑ ልዩ የሕክምና መስታወቶችን (Vials) በሀገር ውስጥ ለማምረት ያስችላል። ይህም የጤናው ዘርፍ ያለበትን የውጭ ግብዓት ጥገኝነት በእጅጉ ይቀንሰዋል።

የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ጉዞ የደቡብ ኮሪያን "መጀመሪያ ብረት" (Steel First) ስትራቴጂን ያስታውሳል። ኮሪያ የፖስኮ (POSCO) የብረት ኩባንያን በመገንባት ለመኪና እና መርከብ ግንባታ ኢንዱስትሪዎቿ መሠረት በመጣል፣ ባህላዊ ዓሣ አጥማጅ የነበሩ መንደሮችን ወደ ዓለም አቀፍ የኢንዱስትሪ ማዕከልነት ቀይራለች።

በተመሳሳይ የቱርክዬ ተሞክሮ የግንባታ ቁሳቁስ ምርት እንዴት የኢኮኖሚ ምሰሶ እንደሚሆን እና ለጠቅላላ ሀገራዊ ምርት (GDP) እስከ 30 በመቶ አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚችል ማሳያ ነው።

ኢትዮጵያም እነዚህን ለኢኮኖሚው መሠረት የሆኑ ማዕድናትን ወደ ምርት በመቀየር፣ በሁለተኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት እና የኢንዱስትሪ ሽግግሯን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሠራች ትገኛለች።

በለሚ ታደሰ