Search

ከመገለል ወደ ማዕከልነት፦ የመጋቢት ለውጥ እና የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ አካታችነት አዲስ ምዕራፍ

እሑድ መጋቢት 20, 2018 196

የመጋቢት 2010 . ለውጥ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ቀደም ሲል የነበረውን የተገደበ እና የተወሰኑ ቡድኖች ብቻ የበላይ የሆኑበትን ሥርዓት በመቀየር ረገድ ትልቅ የታሪክ ምዕራፍ ሆኖ ይመዘገባል።

ይህ ለውጥ በተለይም ለሦስት አሥርተ ዓመታት ያህል "አጋር" በሚል መጠሪያ ከማዕከላዊ የውሳኔ ሰጪነት ሚና ተገልለው የነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ወደ መሐል ያመጣበት ሂደት ዋና መገለጫው ነው።

የፖለቲካ ምኅዳሩን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለተፎካካሪ ኃይሎች ክፍት ለማድረግ የተሞከረበት መንገድም የለውጡ ጉልህ ተግባር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ቀደም ሲል በነበረው የኢሕአዴግ አወቃቀር ውስጥ አራቱ አባል ድርጅቶች ብቻ የሀገራችንን ዕጣ ፈንታ የሚወስኑበት እና "አጋር" ተብለው የሚጠሩት እንደ ሶማሌ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉል-ጉሙዝ፣ ጋምቤላ እና ሐረሪ ያሉ ክልሎች በሞግዚት የሚመሩበት ሥርዓት ሰፍኖ ቆይቷል።

እነዚህ ክልሎች በግንባሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ የመሳተፍም ሆነ የሀገርን ፖሊሲ የመቅረፅ መዋቅራዊ ዕድል አልነበራቸውም።

ይህ መዋቅራዊ መገለል ክልሎቹ የሀገራቸውን የፖለቲካ አቅጣጫ ከመወሰን ይልቅ ተቀባይ ብቻ እንዲሆኑ በማድረጉ፣ ዜጎች በገዛ ሀገራቸው ባይተዋርነት እና የሁለተኛ ዜግነት ስሜት ፈጥሮ የቆየ ሲሆን፣ ለሀገራዊ አንድነት መላላትም እንደ አንድ ምክንያት ሲነሣ ቆይቷል።

ከመጋቢት ለውጥ ማግስት ያለፉ መልካም ሥራዎችን በማቆየት፣ ስህተቶችን ማረም እና የወደፊት ፍላጎቶችን ማሟላት በሚል በመደመር እሳቤ መሪነት ይህንን ታሪካዊ አድልኦ በመሰረዝ ረገድ እንደ አንድ መዋቅራዊ መፍትሔ ቀርቧል።

ይህ ለውጥ ከስም ባለፈ በተግባር የክልሎችን እኩልነት በማረጋገጥ፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ወደ ዳር ተገፍተው የነበሩ ዜጎች ወደ ማዕከላዊ ፖለቲካ እንዲመጡ ተጨባጭ መደላደል ፈጥሯል።

ከዚህ ጎን ለጎን፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለሁሉም ወገኖች ክፍት የማድረጉ ሂደት ሌላው ትልቅ እርምጃ ተደርጎ ይወሰዳል። የለውጡ መንግሥት ለዓመታት በትጥቅ ትግል እና በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩ ድርጅቶችን ከአሸባሪነት ዝርዝሩ በመሰረዝ፣ በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ጥሪ አቅርቧል።

ይህንን ተከትሎም በስደት ይኖሩ የነበሩ የፖለቲካ መሪዎች እና በሺዎች የሚቆጠሩ የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሀገር ቤት በመመለስ በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ መሳተፍ ጀምረዋል።

ይህ እርምጃ ሀገራችን ለዓመታት ታጥራበት የነበረውን የአንድ ፓርቲ የበላይነት በመስበር፣ የተቃውሞ ድምፆች በነፃነት የሚሰሙበት ምኅዳር ለመፍጠር መሠረት ጥሏል።

ይሁን እንጂ ይህ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ምኅዳር የመክፈት ጉዞ ከፈተናዎች ነጻ አልነበረም። የፖለቲካ እስረኞች መፈታት እና በስደት ይኖሩ የነበሩ ኃይሎች ወደ ሀገር ቤት መግባት ትልቅ ተስፋን የፈጠረ ቢሆንም፣ የሀገራችን የፖለቲካ ባህል ከእልህ እና ከግጭት ወደ ውይይት የመቀየር ሥራ አሁንም ትልቅ ትኩረትን የሚሻ ጉዳይ ነው።

መንግሥት ተቋማትን በገለልተኝነት ለመገንባት እና ሁሉንም ወገኖች ለማካተት የወሰዳቸው የምሕረት እርምጃዎች የሚደነቁ ቢሆኑም፤ የተገኘው ዕድል ለዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንዲውል የሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮች ቁርጠኝነት እና የሰላማዊ ትግል ደንቦችን ማክበር ወሳኝ መሆኑን ካለፉት ጥቂት ዓመታት ልምድ መረዳት ይቻላል።

የመጋቢት ለውጥ ያስገኘው ፖለቲካዊ አካታችነት፣ ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር ለጀመረችው ጉዞ እንደ ትልቅ መነሻ የሚያገለግል ታሪካዊ ክስተት ነው።

በለሚ ታደሰ