መጋቢት፣ ለኢትዮጵያውያን የድል መባቻ፣ የነፃነት ቃል-ኪዳን የታደሰበት እና የለውጥ ወጋገን የቀደደበት ወር ነው።
ዛሬ ላይ ቆመን ወደ ኋላ ስንመለከት የምናየው ተመቻችቶ የተዘረጋ ምንጣፍ ሳይሆን እንቅፋቶችን እና መሠናክሎችን በጽናት የረገጠ እና የተረማመደ ታላቅ ሕዝብን እንዲሁም ፈተናን ወደ ዕድል የመቀየር ጥበብን ነው።
ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት ሲያልፍ ይዘነጋ ይሆናል እንጂ፣ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ያለፈችበት ጎዳና ምናልባት አንዳንዶች ቢያልፉበት ኖሮ፣ ዕጣ ፈንታቸው ከእኛ በተቃራኒ መበታተን በሆነ ነበር።
ኢትዮጵያ በመሠረታዊነት ሕልውናዋን የሚፈታተኑ የ"ሦስትዮሽ መከራዎች" (Triple Shocks) ውስጥ አልፋለች፤ እነዚህም፦
· የጥፋት ሴራና ጦርነት፦ ደም አፋሳሽ ጦርነት እና በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች ሀገራዊ አንድነታችንን ለመበጣጠስ፣ ኢኮኖሚያችንን ለማድቀቅ እና ንጹኃንን ለመጨረስ የታለመ የውስጥ እና የውጭ ሴራ ነበር።
· ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ጫና፦ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ያስከተለው የዋጋ ንረት፣ የነዳጅ እና የማዳበሪያ እጥረት እንዲሁም ካለፈው ሥርዓት የተወረሰ የዕዳ ጫና እና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት የሀገራችን መጪ ዘመን አስፈሪ እና ጨለማ እንዲመስል አድርገው ነበር።
· የተፈጥሮ ፈተና፦ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ድርቅ እና የጎርፍ አደጋዎች እንዲሁም የአንበጣ ወረርሽኝ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቻችንን ለፈተና ዳርገው ነበር።
“ኢትዮጵያ ትፈርሳለች” ብለው ያሟረቱ እና በመበታተናችን ሊነግዱ የቋመጡ ሁሉ የኢትዮጵያን አይበገሬነት ዘንግተውት ነበር።
የማይበገረው የኢትዮጵያ ማንነት
እኛ ኢትዮጵያውያን በፈተና ውስጥ የምንጠነክር፣ በእሳት ውስጥ የምናልፍ ወርቆች ነን! ኢትዮጵያ እና ሕዝቧ ፈተናን ወደ ምርታማነት የመቀየር ልዩ ብቃት አላቸው።
ከተረጂነት ወደ ስንዴ ላኪነት፦ በዓለም ፊት "የረሃብ ተምሳሌት" ተብለን እንድንሰደብ ያደረገንን የታሪክ ጠባሳ በመደምሰስ፣ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ዛሬ ስንዴን ወደ ውጭ መላክ ጀምረናል። በ2017/18 የምርት ዘመን የተገኘው 29 ሚሊዮን ቶን ስንዴ የጽናታችን ፍሬ ነው።
የሉዓላዊነት ምልክት (ሕዳሴ ግድብ)፦ በዲፕሎማሲያዊ ጫና እና በገንዘብ እገዳ የሕዳሴው ግድብ እንዳይጠናቀቅ የተደረገውን ሴራ በመበጣጠስ፣ ዛሬ ሥራው ተጠናቅቆ ኃይል ያመነጫል።
ከተሞች በአዲስ ምልከታ፦ አዲስ አበባን ጨምሮ በ75 ከተሞች የተጀመረው የኮሪደር ልማት፣ የከተሞቻችንን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለነዋሪዎች ምቹ እና ውብ አድርጓቸዋል። የፕላስቲክ ቤቶችን በዘመናዊ ሕንፃዎች፣ ጭቃን በብስክሌት መንገድ ቀይረናል።
የኢትዮጵያ ዳግም ትንሣኤ በዓለም መድረክ
ኢትዮጵያ ዛሬም በዓለም ጂኦ-ፖለቲካ ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን እያሳደገች ነው፦
· የብሪክስ (BRICS) አባልነት፦ ከዓለም ግዙፍ ኢኮኖሚዎች ጋር እኩል መቀመጣችን የዲፕሎማሲያዊ ልዕልናችን ማሳያ ነው።
· የባሕር በር ጥያቄ፦ ለዘመናት የታፈነውን የባሕር በር ጥያቄ ወደ ተጨባጭ ዲፕሎማሲያዊ አጀንዳነት አሸጋግረናል።
· ዲጂታል ኢትዮጵያ፦ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶችን በቴክኖሎጂ በማብቃት (5 Million Coders) እና የፋይናንስ ሥርዓታችንን (Telebirr) በማዘመን የነገዋን ብልጽግና ዛሬ ላይ መሠረት ጥለናል።
ለላቀ ድል!
ያለፍንባቸው ፈተናዎች አስከፊ ቢሆኑም፣ ያገኘናቸው ድሎች ግን ከዚያ በላይ ታላቅ ናቸው። ይህ ለውጥ የጥቂቶች ሳይሆን፣ በፈተና ውስጥ ጸንቶ የቆመው የመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ ውጤት ነው።
ዛሬም በሥራ ወዳድነት፣ በፈጠራ እና በላቀ እልህ በመንቀሳቀስ የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ መቀየር ይኖርብናል። ፈተናዎችን ወደ ዕድል፣ ድክመቶችን ወደ ጥንካሬ እየቀየርን ወደ ተሟላ ብልጽግና እንጓዛለን!
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጽናት እና ጥረት ታፍራ እና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች!
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ