የቀድሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የትግራይ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብና ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራ በአዲስ አበባ መጀመሩን አግባብነት ያለው ውሳኔ መሆኑን ገለጹ።
ኮሚሽኑ ከዛሬ መጋቢት 23 እስከ መጋቢት 25 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በሚያካሂደው በዚህ መድረክ ላይ ከትግራይ ክልልና ከአዲስ አበባ የተውጣጡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ወይዘሮ ኬሪያ የሀገራዊ ምክክር መድረኩ ዋና ዓላማ በማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ያሉ ጥያቄዎችና ችግሮች በጦርነትና በጉልበት ሳይሆን በሰላማዊ ውይይት ብቻ እንዲፈቱ ማስቻል መሆኑን አብራርተዋል።
ትግራይ ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች የተለየች አለመሆኗን የገለጹት አፈ-ጉባኤዋ፣ በክልሉ ምቹ ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ በአዲስ አበባ አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራው መቀጠሉ ለሰላም ቅድሚያ የሚሰጥ እርምጃ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ችግሮችን በመመካከር መፍታት ብቸኛው አዋጭ መንገድ መሆኑን በማመን፣ በሰላም የሚያምነው የትግራይ ማኅበረሰብ በአሁኑ ወቅት በመድረኩ ላይ በቀናነትና በንቃት እየተሳተፈ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
የትግራይ ክልል ጥያቄዎች እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሁሉ በመወያየትና በመመካከር ምላሽ የሚያገኙ መሆኑን ወይዘሮ ኬሪያ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ይህ መድረክ የትግራይ ተወላጆች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ይፋዊ አቋም የሚያንጸባርቁበትና ለመፍትሔው የበኩላቸውን የሚያበረክቱበት ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑም ተመላክቷል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።