Search

የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ትንሣኤ፡ ከጥገኝነት ወደ አምራችነት የተደረገው የታሪክ ዝላይ

ቅዳሜ ግንቦት 08, 2018 190

የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ያስመዘገበው እመርታዊ ለውጥ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ መዋቅር ከመሠረቱ እየቀየረ ይገኛል። ይህ አስደናቂ የኢንዱስትሪ ግስጋሴ በዘፈቀደ የመጣ ሳይሆን፣ በጥናት ላይ የተመሠረቱ የፖሊሲ ማሻሻያዎች፣ "መደመር" በተሰኘው ሀገራዊ የፍልስፍና እይታ እና እውነታን መሠረት ባደረገ (Pragmatic) አመራር የተገኘ ትልቅ ሀገራዊ ድል ነው። ኢትዮጵያ ከነበረችበት የጥሬ ዕቃ አቅራቢነት እና የገቢ ምርት ጥገኝነት ወጥታ፣ ወደ አምራችነት እና የቴክኖሎጂ ባለቤትነት ለመሸጋገር የምታደርገው ጥረት በአፍሪካ ደረጃ አርአያነት ያለው ስኬት እያመጣ መሆኑን ተጨባጭ መረጃዎች በግልፅ ያሳያሉ።

የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ጉዞ ስኬት በውል ለመረዳት፣ ዘርፉ ያለፈባቸውን የታሪክ ምዕራፎች መለስ ብሎ መቃኘት ያሻል። በታሪክ ሂደት ውስጥ የታዩት ሥርዓቶች የየራሳቸውን ጥረት ቢያደርጉም፣ ዋነኛው ፈተና የነበረው የጀመሩትን ከዳር የማድረስ የቀጣይነት እጥረት እና የቀደመውን ስኬት የማፍረስ አፍራሽ ዝንባሌ ነበር።

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን፣ የኢንዱስትሪ ልማት መሠረት የተጣለው በዋናነት በውጭ ባለሀብቶች ተሳትፎ ሲሆን በወቅቱ በባቡር መስመር የተሳሰሩ የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴዎች ተፈጥረው 233 መካከለኛና ከፍተኛ ፋብሪካዎች መገንባት ችለው ነበር። ሆኖም የሀገር ውስጥ ባለሀብት ተሳትፎ እጅግ ዝቅተኛ ነበር። የደርግ ሥርዓት ሲመጣ፣ የግል ኢንዱስትሪዎች ወደ መንግሥት ይዞታነት የተዛወሩበትና የካፒታል ገደብ የተጣለበት ዘመን ቢሆንም፣ እንደ አቃቂ መለዋወጫዎች እና ናዝሬት ትራክተር ያሉ ግዙፍ የመሠረታዊ ኢንዱስትሪ ተቋማት መመስረት ችለው ነበር።

በመቀጠል የመጣው የኢህአዴግ ዘመን ደግሞ ትኩረቱን ወደ ውጭ ኤክስፖርት በሚላኩ የጨርቃጨርቅና የቆዳ ምርቶች ላይ በማድረግ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በስፋት ቢገነባም፣ ስልቱ ከፍተኛ የውጭ ዕዳ ክምችትን አስከትሎ አልፏል። ኢንዱስትሪዎቹ ለሚያመርቱት ምርት የሚሆን ጥሬ ዕቃ 90 በመቶ በላይ ከውጭ እንዲያስገቡ ያደረገ በመሆኑ፣ ዘርፉ የውጭ ምንዛሬን ከመፍጠር ይልቅ የሚበላ እንዲሆን አድርጎት ነበር። አሁን ያለው የሪፎርም አመራር እነዚህን መዋቅራዊ ስብራቶች ለመጠገን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምን ተግባራዊ በማድረግ፣ ኢንዱስትሪው በመደመር እሳቤ፣ ተኪ ምርት ላይ በማተኮር እና ከፍተኛ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ራስን ወደ መቻል አቅጣጫ ቀይሯል።

የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን አሁን ላለበት ደረጃ መድረስ እንደ ትልቅ ሚስጥር የሚጠቀሰው የመንግሥትን ሚና ከመፈፀም ወደ አመቻችነት መቀየሩ ነው። የሪፎርሙ መንግሥት የቀደሙ ሥርዓቶች የጀመሯቸውን ስኬታማ ፕሮጀክቶች በማስቀጠል፣ ስህተቶችን በማረም እና አዳዲስ አቅሞችን በመጨመር የታየውን የሃብት ብክነት መቀነስ ችሏል። አመራሩ ከወግ አጥባቂነት እና ከአክራሪ ለውጥ ጽንፎች በመውጣት፣ ስትራቴጂካዊ የሆኑ ዘርፎችን ለገበያ ውድድር ብቻ ሳይተው፣ ራሱ ቀዳሚ ኢንቨስትመንቶችን በማፍሰስ ለግሉ ዘርፍ መነቃቃት መንገድ ጠርጓል።

ኢትዮጵያ አራተኛውን የኢንዱስትሪ አብዮት ለመቀላቀል ዘግይቶ መድረስ ጉዳት አለው የሚለውን እሳቤ በመተው፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና በኤሮስፔስ ቴክኖሎጂዎች ላይ በንቃት መሳተፍ ጀምራለች። እንዲሁም የኢንዱስትሪ ልማት ስልቱ ከተናጠል ፓርኮች እይታ ወጥቶ፣ ምርትን ከሎጂስቲክስ፣ ከደረቅ ወደቦች እና ከባቡር መስመሮች ጋር ወደሚያቀናጅ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጠና መሸጋገሩ ሌላው የትራንስፎርሜሽኑ ቁልፍ ስልት ነው።

"ኢትዮጵያ ታምርት" የተሰኘው ሀገራዊ ንቅናቄ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የታዩትን ማነቆዎች በመለየት እና የተቀናጀ ድጋፍ በማድረግ አስደናቂ ገድል አስመዝግቧል። ከሪፎርሙ በፊት በሀገሪቱ የነበሩ ፋብሪካዎች የማምረት አቅም በአማካይ 46 በመቶ ብቻ የነበረ ሲሆን፣ በቀጣይነት በተደረገው ንቅናቄ ይህ ቁጥር 2018 .. ወደ 66.3 በመቶ ከፍ ብሏል። በተመሳሳይ የፖሊሲ ማሻሻያ፣ ቀደም ሲል ምርት አቁመው የነበሩ 830 ግዙፍ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ የተመለሱ ሲሆን፣ 325 አዳዲስ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ደግሞ ወደ ማምረት ሥራ ገብተዋል። ይህ ከፍተኛ መነቃቃት በዘርፉ 235 ሺህ በላይ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል። የንቅናቄው አንዱ ትልቁ ገድል የገቢ ምርትን መተካት ሲሆን፣ 2018 .. ዘጠኝ ወራት ብቻ 4.85 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ተችሏል።

ኢትዮጵያ በባህላዊ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ብቻ ሳትገደብ፣ የሀገራችንን የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት የሚያረጋግጡ ዘርፎችን መቀላቀሏ ትልቅ የታሪክ እጥፋት ነው። ከግዙፉ የአውሮፕላን አምራች ቦይንግ ጋር በተደረገ ስምምነት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላን መለዋወጫዎችን በሀገር ውስጥ በማምረት ለዓለም አቀፍ አቅርቦት ሰንሰለት እያቀረበ ይገኛል። በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና ዩኒቨርሲቲ መቋቋሙ፣ እንዲሁም አምስት ሚሊዮን ወጣቶችን በዲጂታል ክህሎት የሚያሰለጥነው ፕሮጀክት ሀገሪቱ ለወደፊቱ ላቀደችው የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር ጠንካራ መሠረት ጥሏል።

የኢንዱስትሪ ልማት እንዲፋጠን አስተማማኝ የመሠረተ ልማት ግብዓቶች ማቅረብ ወሳኝ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሁን ላይ 80 በመቶ የሚሆነውን የመሠረተ ልማት ግብዓቶች ከአገር ውስጥ አምራቾች ማግኘት ጀምሯል። በአንድ መንፈቅ ዓመት ውስጥ ብቻ 3,944 ትራንስፎርመሮች፣ 32 ሺህ በላይ የኤሌክትሪክ መከላከያዎች፣ 97 ሺህ በላይ የትራንስፎርመር መከላከያ መሣሪያዎች፣ እንዲሁም 32 ሺህ ሜትር በላይ የኤሌክትሪክ ገመዶች እና ኮንዳክተሮች በሀገር ውስጥ ተመርተዋል። በሌላ በኩል ፀሐይ ኃይል የሚሠሩ፣ CCTV ካሜራዎችን እና 5G ኔትወርክን ያካተቱ ስማርት ፖሎች በሀገር ውስጥ መመረት ጀምረዋል። የነዳጅ ጥገኝነትን ለመቀነስ በተወሰደው እርምጃም በአሁኑ ወቅት 100 ሺህ በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በሀገሪቱ የሚገኙ ሲሆን፣ ይህም ኢትዮጵያን በአረንጓዴ ኢኮኖሚ የአፍሪካ ተምሳሌት አድርጓታል።

የማዕድን ዘርፉም ለኢንዱስትሪ ልማቱ ዋነኛ የጥሬ ዕቃ ምንጭ እና የውጭ ምንዛሬ መገኛ እንዲሆን የተደረገ ሲሆን፣ ለኤክስፖርት የቀረበው የወርቅ ምርት 2010 እስከ 2017 .. ባለው ጊዜ ውስጥ 1241.4 በመቶ እምርታዊ ዕድገት አሳይቷል። በተመሳሳይ የድንጋይ ከሰል የሀገር ውስጥ የገበያ ድርሻ 2010 .. ከነበረበት 17 በመቶ 2017 .. ወደ 75 በመቶ ከፍ ብሏል። በኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝን በመጠቀም ግዙፍ የማዳበሪያ ፕሮጀክቶች የተጀመሩ ሲሆን፣ ምርት አቁመው የነበሩ የስኳር ፋብሪካዎችም ወደ ምርት ተመልሰው ሀገሪቱን በዘርፉ ራስን ወደ መቻል አሸጋግረዋታል።

እነዚህ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች በሀገሪቱ ማክሮ-ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ ተፅዕኖ አሳርፈዋል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት 2010 .. 8 ቢሊዮን ብር ኪሳራ አስመዝግበው የነበሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ በሪፎርሙ አማካኝነት 2018 .. የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም 351 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘት ችለዋል። 2002 እስከ 2009 .. 15.6 ቢሊዮን ዶላር የነበረው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት፣ 2010 እስከ 2018 .. ባሉት ዓመታት ወደ 31 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል። 2010 .. 4.8 በመቶ የነበረው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ዕድገት 2018 .. ወደ 13 በመቶ ያደገ ሲሆን፣ የውጭ ዕዳ ከሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት የነበረው ድርሻም 30.6 በመቶ ወደ 26.9 በመቶ ዝቅ ማለት ችሏል።

ምንም እንኳን ይህ ሁሉ አስደናቂ ስኬት ቢመዘገብም፣ የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና በግብርናው ዘርፍ የሚመረቱ ምርቶች ለኢንዱስትሪዎች በግብዓትነት የመቅረብ ሂደት ክፍተቶች አሁንም ተግዳሮቶች ናቸው። መንግሥት ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት የኢንዱስትሪ ትስስር ስትራቴጂ ቀርጾ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን፣ በተለይ ስድስት ንዑስ ዘርፎችን ትኩረት በማድረግ ከግብርና እና ከማዕድን ጋር ያላቸውን ትስስር እያጠናከረ ይገኛል። ኢትዮጵያ 2030 የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት የመሆን እና 2045 ከዓለማችን 10 ግዙፍ ኢኮኖሚዎች አንዷ የመሆን ራዕይ ሰንቃለች። ይህ ጉዞ ሀገሪቱ ትናንት ታላቅ እንደነበረች፣ ዛሬም በጽናት እየሠራች እንደሆነ እና ነገ ደግሞ ከዚያ በላይ እንደምትሆን በተግባር የሚያረጋግጥ ብሩህ ተስፋ ነው።

 

በአዶንያስ /አረጋይ