በመደመር ፍልስፍና የሚመራው የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያስመዘገባቸው ስኬቶች ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነት እና ስልታዊ አስፈላጊነት በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው።
ኢትዮጵያ እና አሜሪካ፡ "ትክክለኛው ጊዜ …!"
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የተመራው የልዑካን ቡድን በአሜሪካ ያደረገው ቆይታ እና የተከናወኑ ተግባራት ለዚህ ትልቅ ማሳያ ይሆናሉ።
በተለይም አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጥላው የነበረውን የጦር መሣሪያ ሽያጭ ማዕቀብ (ITAR) ማንሳቷ፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው ግንኙነት ወደ አዲስ የደኅንነት እና የስትራቴጂክ አጋርነት መሸጋገሩን ያመለክታል።
ይህ ውሳኔ ሀገራችን በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት የምታደርገውን ጥረት ዕውቅና የሰጠ ነው። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ እና ቀይ ባሕር ቀጣና ሰላም ያላትን የማይተካ ሚና በግልጽ ተናግረዋል።
የሁለትዮሽ መዋቅራዊ ምክክር ማዕቀፍ (Bilateral Structured Dialogue Framework) መፈረሙ ደግሞ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በደኅንነት ዘርፎች የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ነው።
ይህን አስመልክተው በኤክስ ገጻቸው ሰፋ ያለ አስተያየታቸውን ያጋሩት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገ/ማርያም የኢትዮጵያ እና አሜሪካ ግንኙነት አሁን አዲስ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ጠቁመዋል።
ይህን ጊዜ ሲጠብቁት እና ሲሠሩለት እንደኖሩ የሚጠቅሱት ፕሮፍሰሩ፣ "ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ ሁልጊዜም ትክክለኛው ጊዜ ነው! የአሜሪካ እና የኢትዮጵያን ግንኙነት በትክክለኛው መንገድ ለማስኬድ ደግሞ ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው!" በማለት ሀሳባቸውን አስፍረዋል።
የቀይ ባሕር ራዕይ እና የዓለም አቀፍ ምሁራን ድጋፍ
የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥረት አሁን ላይ ከብሔራዊ ፍላጎት አልፎ ቀጣናዊ ፋይዳ እንዳለው በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንዛቤ እየተያዘበት መጥቷል።
የተለያዩ የአሜሪካ የጥናት ተቋማት እና ወታደራዊ መሪዎች ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶች ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆን እንዳለባት እያሳሰቡ ይገኛሉ።
የአሜሪካው ጄኔራል ማይክል ላንግሌ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ተደራሽነት ማግኘቷ ለቀጣናው ሰላም ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
ይህም ምስራቅ አፍሪካዊቷ ኃይል የምትከተለው የተግባራዊ ሉዓላዊነት ጽንሰ-ሀሳብ በአጋርነት እና በሕግ ማዕቀፍ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ለጎረቤት ሀገራት ስጋት ሳይሆን የጋራ ዕድገት ምንጭ መሆኑን ያስመከረበት ስኬት ነው።
የብሪክስ አባልነት እና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ከፍታ
ኢትዮጵያ በሕንድ በተካሄደው የብሪክስ የሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ ያሳየችው ንቁ ተሳትፎ፣ የአፍሪካዊቷን ምሰሶ በባለብዙ ወገን ግንኙነት ግንባታ ውስጥ ያላትን ሚና ያረጋገጠ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤስ ጃይሻንካር ጋር ያደረጉት ውይይት የደቡብ-ደቡብ ትብብርን ለማጠናከር ያለመ ነው።
ኢትዮጵያ በብሪክስ አባልነቷ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ እና የፖለቲካ ተቋማት ውስጥ የአፍሪካ ድምፅ ሆና የወጣችበት ነው። ይህም ፍትሃዊ የዓለም አስተዳደር እንዲሰፍን ለምታደርገው ጥረት ትልቅ ስልታዊ ድል ተደርጎ ይወሰዳል።
ከተመድ 80ኛ ዓመት እስከ አፍሪካ ፎርዋርድ፡ የአፍሪካ ድምፅ መሆን
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ80ኛ ዓመት ምሥረታ በዓል በአዲስ አበባ መከበሩ፣ ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም የከፈለችውን መስዋዕትነት የሚዘክር ነው።
ለበዓሉ መታሰቢያ የወጡት አራት ቴምብሮች፣ ባለታሪኳ ምድር ከተመድ ምሥረታ ጀምሮ የነበራትን ሚና እና በሰላም ማስከበር ስምሪት ያሳየችውን ጀግንነት ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተቋማት ፍትሃዊ እንዲሆኑ ከድርጅቱ ምሥረታ አሥርተ ዓመታት ቀድማ በመንግሥታቱ ማኅበር ጭምር ድምጿን ስታሰማ ቆይታለች።
የቀድሞው የመንግሥታቱ ማኅበር የሁለተኛውን ዓለም ጦርነት መቆጣጠር ባለመቻሉ የመፍረስ አደጋ ሲጋረጥበት የኢትዮጵያ ጥያቄዎች ትክክለኛ መሆናቸው በተግባር ተረጋግጧል።
ለዚህም ነው ያላትን የሞራል የበላይነት ተጠቅማ አፍሪካ በመንግሥታቱ ድርጅት ውስጥ ፍትሃዊ ውክልና እንድታገኝ ማሳሰቧን የቀጠለችው።
በ80ኛው ዓመት አከባበር ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኩል የተላለፈው መልእክትም፣ አፍሪካ የቋሚ የጸጥታው ምክር ቤት መቀመጫ እንዲሰጣት የምታደርገውን ግፊት ያጠናክረዋል።
ከተመድ 80ኛ ዓመት አከባበር ቀደም ብሎ በናይሮቢ በተካሄደው "አፍሪካ ፎርዋርድ" ጉባኤ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያደረጉት ንግግር አፍሪካ ከእርዳታ ተቀባይነት ወጥታ ወደ እውነተኛ አጋርነት መሸጋገር እንዳለባት ያሳሰበ ነበር።
የአፍሪካ ፎርዋርድ (Africa Forward) ጽንሰ-ሀሳብ አፍሪካ ከርዳታ ጠባቂነት ወጥታ የዓለም የኢኮኖሚ ሞተር የመሆን ራዕይ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ከብሔራዊ ፍላጎቷ እና ለአፍሪካ መጻኢ ዕድል ካላት መሻት ጋር አያይዛ ሀሳቧን አቅርባለች።
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ጉብኝት እና የአጋርነት ማሳያ
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ ያደረጉት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት፣ የኢትዮጵያ እና ፈረንሳይን ስልታዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግሮታል።
ይህ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ በትብብር የቆየው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በየጊዜው በተጨባጭ ውጤቶች ታጅቦ መቆየቱን ነው የፕሬዚዳንት ማክሮን ጉብኝት ያረጋገጠው።
በጉብኝቱ ወቅት የተፈረሙት ስምምነቶች፣ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ በትብብር የቆየውን ግንኙነት በፀና መሰረት ላይ ያቆሙ ናቸው።
ትብብሩ የፈረንሳይ ታላላቅ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸውን እምነት የሚያሳይ ሲሆን፣ ባለታሪኳ ምድር በታዳሽ ኃይል እና በቴክኖሎጂ ለጀመረችው ጉዞ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው።
በአጠቃላይ እነዚህ ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶች ኢትዮጵያ የነበረባትን ጫና ተቋቁማ ለቀጣናው ሰላም እና ለዓለም አቀፍ ትብብር ያላትን ቁልፍ ሚና ያስመሰከረችባቸው ናቸው።
በለሚ ታደሰ