Search

ከሕልም ወደ ገቢር - ኢንዱስትሪን ስትራቴጂያዊ በሆነ መንገድ መምራት

ዓርብ ግንቦት 07, 2018 110

ኢትዮጵያ ለዘመናት የተፈጥሮ ሀብት የታደለች ነገር ግን ተገቢውን ጥቅም የማታገኝ ሀገር እና በከፍተኛ ደረጃ የገቢ ምርት ጥገኝነት ሰንሰለት ውስጥ ታስራ ቆይታለች።
 
ይሁን እንጂ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ይህ ታሪክ በከፍተኛ ፍጥነት እየተቀየረ ይገኛል።
 
የዚህ ታላቅ ለውጥ ማዕከል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ይዘውት የመጡት "መደመር" የተሰኘው ሀገራዊ ፍልስፍና እና ገቢር ነበብነትን" የተላበሰ የኢኮኖሚ አመራር ነው። ይህ ጉዞ ኢትዮጵያን ከአቧራ ወደ ዐሻራ፣ ከሸማችነት ወደ አምራችነት ያሸጋገረ አስደናቂ ትርክት የያዘ የለውጥ ምዕራፍ ነው።
 
መዋቅራዊ ስብራትን በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መጠገን
የለውጥ አመራሩ ሥልጣን ሲረከብ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ በከፍተኛ ዕዳ የተተበተበ፣ ለምርት የሚሆን ጥሬ ዕቃን 90 በመቶ ከውጭ የሚያስገባ እና የማምረት አቅሙ ከ46 በመቶ ያልበለጠ ደካማ ቁመና ላይ ነበር።
 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን መዋቅራዊ ስብራት ለመጠገን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምን ቀረጹ። የዚህ ስልት ቀዳሚ ምሥጢር "መደመር" ሲሆን፣ ትርጉሙም የቀደሙ ሥርዓቶች የጀመሯቸውን ስኬታማ ፕሮጀክቶች ካሉበት በማስቀጠል፣ ስህተቶችን በማረም እና አዳዲስ የቴክኖሎጂ አቅሞችን በመጨመር ላይ የተመሠረተ ነው።
 
ይህ ስትራቴጂያዊ ዕይታ ወደ ተግባር ሲቀየር "ኢትዮጵያ ታምርት" የተሰኘው ሀገራዊ ንቅናቄ ተወለደ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግንባር ቀደምትነት የመሩት ይህ ንቅናቄ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የታዩትን ማነቆዎች በመለየት እና የተቀናጀ ድጋፍ በማድረግ አስደናቂ ውጤት አስመዝግቧል።
 
በዚህም ሳቢያ ከለውጡ በፊት 46 በመቶ የነበረው የፋብሪካዎች የማምረት አቅም አጠቃቀም በ2018 በጀት ዓመት ወደ 66.3 በመቶ ከፍ ብሏል። ይህም ማለት ኢትዮጵያ የነበራትን ያልተጠቀመችበትን አቅም በሃያ በመቶ በላይ አሳድጋለች። ንቅናቄው 830 ምርት አቁመው የነበሩ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ የመለሰ ሲሆን፣ 325 አዳዲስ ግዙፍ ፋብሪካዎችም ገበያውን እንዲቀላቀሉ አድርጓል።
 
የቀድሞ መድረስ ሽልማት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ የተከተሉት ሌላው ምሥጢራዊ ስልት "የቀድሞ መድረስ ሽልማት" (Early Bird Reward) ነው። ኢትዮጵያ በሌሎች የኢንዱስትሪ ዘርፎች የባከነባትን ጊዜ ለማካካስ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ገና በማደግ ላይ ባሉ ከፍተኛ ቴክኖሎጂዎች ላይ በንቃት እንድትሳተፍ አድርገዋል።
 
ለዚህም ትልቁ ማሳያ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ኢንስቲትዩት መቋቋም እና በዓለም ሁለተኛ የሆነው የAI ዩኒቨርሲቲ ግንባታ መጠናቀቅ ነው። ይህ ስልት ኢትዮጵያን ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ባለፈ ወደ ቴክኖሎጂ አምራችነት እና የአፍሪካ የዲጂታል ማዕከልነት እያሸጋገራት ይገኛል።
 
ኢትዮጵያ ከአውሮፕላን ገዥነት ወደ አውሮፕላን መለዋወጫ አምራችነት መሸጋገሯ ደግሞ ሌላኛው ታላቅ ገድል ነው። ከቦይንግ (Boeing) ኩባንያ ጋር በተደረገ ስትራቴጂያዊ ስምምነት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላን መለዋወጫዎችን (Aerospace parts) በሀገር ውስጥ ማምረት ጀምሯል።
 
ይህ ፋብሪካ እንደ "ኢንሱሌሽን ብላንኬት" እና "ኤሌክትሪካል ዋየር ሃርነስ" ያሉ ክፍሎችን በማምረት ለዓለም አቀፉ ገበያ ማቅረብ መጀመሩ የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ሉዓላዊነት ያረጋገጠ ኩራት ነው።
 
የገቢ ምርትን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት
 በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ሌላው የተመዘገበው እመርታ የገቢ ምርትን በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ስኬት ነው። ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 4.85 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ተችሏል። አሁን ላይ 100 በመቶ የሚሆነውን የወታደራዊ እና የፖሊስ አልባሳት፣ እንዲሁም የቢራ ብቅል በሀገር ውስጥ ማምረት ተችሏል።
 
በተጨማሪም፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሁን ላይ 80 በመቶ የሚሆነውን የመሠረተ ልማት ግብዓቶች ማለትም ትራንስፎርመሮችን፣ የኤሌክትሪክ ገመዶችን እና ኮንዳክተሮችን ከሀገር ውስጥ አምራቾች ማግኘት ጀምሯል። የቦሌ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ ያመረታቸው በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ "ስማርት ፖሎች" የቴክኖሎጂ ሽግግሩ ምን ያህል ዝቅ ብሎ ወደ ወጣቱ መውረዱን ያሳያሉ።
 
የተቀናጀ የኢነርጂ፣ የማዕድን እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት
 የኢንቨስትመንት እና የማዕድን ዘርፉም ከኢንዱስትሪው ጋር በተቀናጀ መልኩ እንዲለማ ተደርጓል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለፍጻሜ በማብቃት እና እንደ ኮይሻ ያሉ ግዙፍ የኃይል ማመንጫዎችን በማጠናቀቅ፣ ለኢንዱስትሪው አስተማማኝ ኃይል እንዲቀርብ አድርገዋል።
 
የማዕድን ዘርፉም የወርቅ ኤክስፖርትን በ1241.4 በመቶ በማሳደግ እና የድንጋይ ከሰል ምርትን ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ግብዓት በማድረግ የውጭ ምንዛሬን ታድጓል። በኦጋዴን የሚገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ በመጠቀም ከዳንጎቴ ጋር በ2.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እየተገነባ ያለው የማዳበሪያ ፋብሪካ ደግሞ ኢትዮጵያን በግብርናው ዘርፍ ሙሉ በሙሉ ራሷን እንድትችል የሚያደርጋት ታሪካዊ ፕሮጀክት ነው።
 
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከነበረባቸው የተናጠል ዕይታ ወጥተው፣ ከሎጂስቲክስ እና ከደረቅ ወደቦች ጋር ወደተሣሠሩ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች (Special Economic Zones) መሸጋገራቸው ለምርቶች ተወዳዳሪነት ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
 
እንደ ድሬዳዋ እና ገዳ (Geda) ያሉ ቀጣናዎች የምርት ወጪን በመቀነስ የኢትዮጵያን ስም በዓለም ገበያ ከፍ አድርገዋል። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አብዮት ደግሞ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከ100 ሺህ በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በሀገሪቱ መንገዶች ላይ መገኘታቸው ለዚህ ማረጋገጫ ነው።
 
ባለፉት ስድስት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራው የኢንዱስትሪ ጉዞ ከቃላት ባለፈ በተግባር የታጀበ ነበር። የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከ8 ቢሊዮን ብር ኪሳራ ወደ 351 ቢሊዮን ብር ትርፍ መሸጋገራቸው የሪፎርሙን ፋይናንሳዊ ስኬት ያረጋግጣል።
 
ይህ የለውጥ ጉዞ ኢትዮጵያ በ2030 የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት፣ በ2045 ደግሞ ከዓለማችን 10 ግዙፍ ኢኮኖሚዎች አንዷ ለመሆን የሰነቀችውን ራዕይ ለማሳካት ጽኑ መሠረት ጥሏል።
 
"ኢትዮጵያ ታምርት" የሚለው ቃል ዛሬ መፈክር ብቻ ሳይሆን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል ያገኙበት፣ የሀገር ውስጥ ምርቶች ገበያውን የተቆጣጠሩበት እና የኢትዮጵያ ክብር በኢንዱስትሪው ዘርፍ ዳግም የታወጀበት አስደናቂ ገድል ነው።
 
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
 
#EBC #Ethiopia #industry #industrialparks #madeinethiopia