የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተመሠረተበትን 80ኛ ዓመት በምናስብበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላምና ለሰው ልጆች መብት መከበር የከፈለችውን መተኪያ የሌለው መስዋዕትነት ማስታወስ ተገቢ ይሆናል፡፡
ሀገራችን ለዓለም አቀፍ ፍትሃዊ ሥርዓት ከመሟገት ባለፈ፣ በተግባር ሕይወቷን የገበረችበት የቆየ ታሪክ አላት።
በድርጅቱ 80ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ላይም፣ ኢትዮጵያ የሞራል ልዕልናዋን በሚመጥን መልኩ የዓለም አቀፍ ተቋማት ፍትሃዊ ውክልና እንዲኖራቸው ጥሪዋን በድጋሚ አድሳለች።
የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጉዞ በቃላት ድርድር ሳይሆን በተግባር በተረጋገጡ ታሪካዊ ክንውኖች የታጀበ ነው።
በታሪኳ ያሳለፈቻቸው ፈተናዎችና የተቀዳጀቻቸው ድሎች ለራሷ ሉዓላዊነት ብቻ ሳይሆን፣ ለመላው ጥቁር ሕዝብና ለተገፉ ወገኖች ሁሉ የሞራልና የፍትህ መሠረት ሆነው አገልግለዋል።
የጄኔቫው ትንቢታዊ ማስጠንቀቂያ እና የዓለም ሕሊና ፈተና
ኢትዮጵያ ለመንግሥታቱ ማኅበር (League of Nations) ያቀረበችው አቤቱታ በዓለም ዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ የፍትህ መጓደልን ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ክስተት ነበር።
የፋሽስት ሞሶሎኒ ጦር ኢትዮጵያን የወረረው የወቅቱን ዓለም አቀፍ ሥርዓት ሕግጋት በመጣስ ነበር፡፡
በ1936 እ.ኤ.አ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በጄኔቫ ተገኝተው “በዓለም ላይ ሕዝብን ለማጥፋት እንዲህ ያለ አሰቃቂ ድርጊት ተፈጽሞ አያውቅም” በማለት የፈጸሙት ንግግር፣ የኃያላኑን ዝምታና የሕግ ክፍተቱን ለዓለም ያጋለጠ ነበር።
“ዛሬ ለእኛ የሆነው ነገ ለእናንተ ይሆናል” የሚለው ትንቢታዊ ንግግራቸው፣ ኃያላን ሀገራት ለሕግና ለፍትህ ካልተገዙ ዓለም ወደ ከፋ መከራ እንደምትገባ ያስጠነቀቀ ነበር።
ያ ማስጠንቀቂያ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መፈንዳት እውን ሆኗል።
ይህ አቋም አፍሪካዊቷ የነጻነት ተምሳሌት ለዓለም የጋራ ደኅንነት መርህ የከፈለችው ታላቅ የዲፕሎማሲ መስዋዕትነት ነው።
በሳን ፍራንሲስኮ የተዘራው የእኩልነት ዘር
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት አብቅቶ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሲመሠረት ኢትዮጵያ ከ51ዱ መሥራች ሀገራት አንዷ በመሆን ታሪካዊ አሻራዋን አኑራለች፡፡
የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በድርጅቱ ቻርተር ዝግጅት ወቅት የሀገራትን የሉዓላዊነት እኩልነት የሚያረጋግጠው አንቀጽ 2(1) እንዲካተት ያደረገው ትግል የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያ "የሥልጣኔ ደረጃ" በሚል ሰበብ ይደረግ የነበረውን አድሏዊ አሠራር በመቃወም፣ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ በእኩልነት እንዲታዩ ያደረገችው ተጋድሎ የላቀ የሰብዓዊ መብት ጥብቅና ማሳያ ነው፡፡
በተጨማሪም በቻርተሩ አንቀጽ 55 ላይ የሰብአዊ መብቶችና የኢኮኖሚ ትብብር ድንጋጌዎች እንዲካተቱ በማድረግ፣ ዓለም አቀፍ ፍትህ ያለ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እኩልነት እንደማይረጋገጥ በተግባር አሳይታለች።
ከቃላት ባለፈ የተሰጠ የነጻነት ድጋፍ
የኢትዮጵያ የፍትህ ጉዞ በቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር ለነበሩ አፍሪካውያን እና በአፓርታይድ ለሚሰቃዩ ታጋዮች መጠጊያ በመሆንም ይገለጻል።
እ.አ.አ በ1960 በዓለም አቀፍ የፍትህ ፍርድ ቤት (ICJ) በአፓርታይድ ሥርዓት ላይ የመሠረተችው ክስ የአፍሪካን ነጻነት እንደ ራሷ ጉዳይ እንደምትመለከተው ያሳያል፡፡
የዚምባብዌው ‘ZANU’ እና የናሚቢያው ‘SWAPO’ ታጋዮች ያገኙት የነበረው ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍም የዚሁ ቆራጥ አቋም ውጤት ነው።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሰላም ጥበቃ ሥራዎች ላይ ያላት ሚና በመስዋዕትነት የተገነባ ነው።
ከ1950ዎቹ የኮሪያ ጦርነት ጀምሮ በኮንጎ፣ በሩዋንዳ፣ በቡሩንዲ እና በሱዳን የታየው ጀግንነት “ሕዝብንና ሀገርን ከራስ ማስቀደም” ከሚለው የወታደራዊ ስነ-ምግባር መርህ የሚቀዳ ነው፡፡
በተጨማሪም እስካሁን ከ100 ሺህ በላይ ወታደራዊና ፖሊስ አባላትን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተልዕኮዎች ማሰማራቷ፣ ሀገራችን ለዓለም ሰላም ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት ያረጋግጣል።
የሩዋንዳው መሪ ፖል ካጋሜ ሀገራቸው በወደቀችበት አስከፊ ወቅት ኢትዮጵያ ለሰጠችው ድጋፍ የገለጹት አድናቆት፣ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች የርህራሄና የፍትህ ተምሳሌት መሆናቸው ምስክር ነው።
ለፍትሃዊ ውክልና የሚደረግ ትግል
ዛሬም ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ውስጥ አፍሪካ ቋሚ መቀመጫ ሊኖራት ይገባል የሚለውን ጥያቄ በግንባር ቀደምትነት እያነሳች ትገኛለች፡፡
ይህ ጥያቄ የዲፕሎማሲያዊ ንግግር ማሟያ ሳይሆን ከዘመናት የፍትህ ተሟጋችነቷ ጋር የተሳሰረ የቆየ አቋም ነው፡፡
አፍሪካ በጋራ የደረሰችበትን የኢዙልዊኒ ስምምነት በጽኑ የምትደግፈው ኢትዮጵያ፣ ዓለም አቀፍ ውሳኔዎች ያለ አፍሪካ ተሳትፎ መወሰናቸው ታሪካዊ ስህተት መሆኑን ትከራከራለች።
ይህ ጥያቄ ከ1936ቱ የመንግሥታቱ ማኅበር ውድቀት የተማረችውና በ1945 የቻርተሩ መሥራች በመሆን የገነባችው የፍትህ እሴት ውጤት ነው።
ኢትዮጵያ ዛሬም ለዓለም አቀፍ ተቋማት ማሻሻያ የምትሟገተው የሰው ልጆች ሁሉ ድምጽ በእኩልነት እንዲሰማ እና የጋራ ብልጽግና እንዲረጋገጥ ካላት ጽኑ ራዕይ በመነሳት ነው።
በለሚ ታደሰ