Search

ሀገራዊ ምክክር፦ ከውጥን እስከ ተስፋ - ለሀገራዊ መግባባት የሚደረግ ታሪካዊ ጉዞ

ዓርብ ግንቦት 07, 2018 148

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ትልቅ ተስፋ የተሰነቀበት እና ለሀገር ግንባታ ወሳኝ ምዕራፍ ተደርጎ የሚወሰድ ተቋም ነው።

ኮሚሽኑ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ያከናወናቸው ተግባራት እና ወደፊት የሚጠብቀው ጉዞ፣ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚኖራቸው ፋይዳ እጅግ የላቀ ነው።

ይህ ታሪካዊ ሂደት ኢትዮጵያ ካለችበት የፖለቲካ ቀውስ ወጥታ ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የምትሻገርበት ድልድይ ተደርጎ ይታመናል።

የኮሚሽኑ መሠረታዊ ዓላማ

ኮሚሽኑ በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 መሠረት ሕጋዊ ሰውነት ያገኘው፣ በፖለቲካ ልሂቃንና በሕዝቡ መካከል የሚስተዋሉ መሠረታዊ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ለመፍታት ነው።

ዋነኛ ግቡም በሀገራችን ስር የሰደዱና ለዘመናት የቆዩ የቅራኔ ምንጮችን በጥናትና በሕዝባዊ ተሳትፎ በመለየት፣ ብሔራዊ መግባባትን ማምጣት፣ ማኅበራዊ መተማመንን ማደስ እና የሀገርን አንድነት በጽኑ መሠረት ላይ መገንባት ነው።

ኮሚሽኑ የሐሳብ የበላይነት የሚነግሥበት፣ ነፃ፣ ገለልተኛ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የውይይት መድረክ የመፍጠር ከባድ አደራ ተጥሎበታል።

ይህ ሂደት ‘አሸናፊ እና ተሸናፊ' ካለበት የፖለቲካ ባህል ወጥተን፣ በጋራ የምናሸንፍበትን መንገድ ለመቀየስ ያለመ ነው።

እስካሁን የተጓዘባቸው ስኬታማ እርምጃዎች

ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ የዝግጅት እና የትግበራ ምዕራፎችን ተሻግሯል። እስካሁን ባለው ሂደት በአብዛኞቹ የክልል መንግሥታት እና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የሕዝብ ተሳትፎ የታከለበት የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የተወካዮች ልየታ ተግባርን በስኬት አጠናቅቋል።

በዚህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ለሀገር ግንባታ እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን እና የመፍትሔ ሐሳቦችን በነፃነት እንዲያንጸባርቁ ዕድል ተፈጥሯል።

ይህ ተሳትፎ በሀገር ውስጥ ብቻ የተገደበ ሳይሆን በደቡብ አፍሪካ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በካናዳ፣ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች እና በአውሮፓ ሀገራት የሚኖሩ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላትንም ያካተተ ነበር።

የትግራይ ክልልን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባትም፣ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከሲቪክ ማኅበራት ጋር በመቀናጀት የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረኩ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ተደርጓል።

ይህም ሂደቱ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ለማካተት ያለውን ጽኑ ፍላጎት የሚያሳይ ነው።

ፈተናዎችን የመሻገሪያ ጥበብ

የኮሚሽኑ ጉዞ አልጋ በአልጋ አልነበረም። በተለይም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እንዳይራመድ እንቅፋት ሆነዋል።

አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች እና የታጠቁ ቡድኖች በሂደቱ ላይ ያላቸው ጥርጣሬ እና ራሳቸውን ማግለላቸውም ሌላኛው ፈተና ነው።

ሆኖም ኮሚሽኑ "በሩ ለማንኛውም ወገን ክፍት ነው" የሚል ጽኑ አቋም በመያዝ፣ እነዚህን አካላት ወደ ሰላማዊ መድረክ ለማምጣት ጥረቱን ቀጥሏል።

አካታችነትን ለማረጋገጥም ከአካል ምክክር በተጨማሪ በአጭር መልዕክት፣ በስልክ፣ በኢ-ሜይል እና በፖስታ አማካኝነት ዜጎች ድምፃቸውን እንዲያሰሙ እና አጀንዳዎቻቸውን እንዲልኩ አመቺ የቴክኖሎጂ ሁኔታዎችን ፈጥሯል።

ቀጣይ ምዕራፎች- ወደ ታላቁ ጉባኤ

የፀጥታ ስጋቶችን እና የቀሩ ሰፊ ተግባራትን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኮሚሽኑን የሥራ ዘመን አራዝሟል።

ይህም ሥራው በጥራት እና በጥልቀት እንዲከናወን ዕድል ይሰጣል። በቀጣዮቹ ወራትም የተሰበሰቡ አጀንዳዎች በባለሙያዎች ተለይተው እና ተቀናጅተው ለታላቁ ሀገራዊ ጉባኤ ይቀርባሉ።

ከዚህ ታሪካዊ ጉባኤ የሚገኙ የጋራ ስምምነቶችም ለመንግሥት አካላት በፖሊሲ ምክረ-ሐሳብነት የሚቀርቡ ሲሆን፣ አፈጻጸማቸውን የሚከታተል እና ተግባራዊነታቸውን የሚያረጋግጥ ሥርዓትም እንደሚዘረጋ ይጠበቃል።

የሰላም ትርፍ

የሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ መሆን ለኢትዮጵያ የሕልውና ያህል የሚታይ ፋይዳ አለው።

ለዘመናት የቆዩ ልዩነቶችን በሠለጠነ መንገድ በውይይት በመፍታት ለዘላቂ ሰላም እና ለጠንካራ ሀገር ግንባታ መሠረት ይሆናል።

የምክክር ሂደቱ በስኬት መጠናቀቅ በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት የተፈጠሩ ቅራኔዎችን ወደ መድረክ በማምጣት ሕዝቡ የጋራ አቋም እንዲይዝባቸው ያደርጋል።

በዚህም መሠረት የሽግግር ፍትሕ ሥርዓቱን በማገዝ በታሪክ ሂደት የተጎዱ ወገኖች ተክሰውና ታርቀው ለቀጣይ የጋራ ሀገር ግንባታ መሠረት የሚጣል ይሆናል።

ግጭቶች በውይይት ሲፈቱ የሚገኘው የሰላም ትርፍ ሀገራችን የሕዝቧን ሰላም እና አንድነት አጠናክራ ወደ ፊት እንድትጓዝ ሰፊ ዕድል ይሰጣል።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጉዞ በፈተናዎች አልፎ እዚህ ቢደርስም፣ ሂደቱ የሚያመጣው ውጤት ግን ኢትዮጵያን ካለችበት የፖለቲካ እና የፀጥታ ቀውስ አውጥቶ ወደ ተሻለ ብሔራዊ መግባባት እና ዕድገት ሊያሸጋግር የሚችል ብርቅዬ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።

ይህ አጋጣሚ እንዳያመልጠን የሁላችንም ንቁ ተሳትፎና ቅንነት ወሳኝ ነው።

በለሚ ታደሰ