Search

የሀገር ግንባታ ሒደት ትናንትን በቅጡ የሚያወሳ፣ ነገን ደግሞ የሚሠራ መሆን አለበት - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ቅዳሜ መጋቢት 26, 2018 72

የሀገር ግንባታ ሒደት ትናንትን በቅጡ የሚያወሳ፣ ነገን ደግሞ የሚሠራ መሆን እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ የስፖርት ፓርክ ዛሬ ሲመረቅ ፣ የሀገር ግንባታ ሥራ ሁለት ዋነኛ ምሰሶዎችን መያዝ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
በአንድ በኩል ትናትንትን በወጉ እና በቅጡ የሚያስታውስ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ነገን ታሳቢ ያደረገ ሥራ በትውልዱ ላይ መሠራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየምን የመሳሰሉ ሥራዎች ጀግኖቻችንን እና ትላንታችንን እንድናስታውስ የሚያደርጉን ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ብቻውን በቂ ባለመሆኑ ነገን በልጆቻችን ላይ መሥራት የግድ ይላል ብለዋል፡፡
መንግሥት ባለፉት ስምንት ዓመታት ወደ 35 ሺህ ገደማ መዋዕለ ሕጻናትን መገንባቱን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በእነዚህ ዓመታት ከታች በሚያድገው ትውልድ ላይ ትኩረት መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
ትኩረትን ዐዳጊ ልጆች ላይ በማድረግ መሥራት ይበልጥ አዋጭ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አክለውም "ከመዋዕለ ሕጻናት እስከ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በስፋት ስንገነባ ልጆች በየሒደቱ እየበቁ በመሄድ ኢትዮጵያ ቀና እንድትል የሚያደርግ አቅም ይዘው ይነሳሉ" ብለዋል፡፡
 
በለሚ ታደሰ