Search

በኦሎምፒክ መድረክ 24 የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያስመዘገቡት 15ቱ የኢትዮጵያ ፈርጦች

እሑድ መጋቢት 27, 2018 176

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ስሟ በክብርና በግርማ ሞገስ እንዲነሳ ካደረጉት ታላላቅ እሴቶቿ መካከል አትሌቲክስ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።

ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በኦሎምፒክ መድረክ ሰንደቅ ዓላማዋን ከፍ አድርገው በማውለብለብ፣ የሀገራችንን ገጽታ በመገንባትና ሕዝባዊ ዲፕሎማሲን በማጠናከር የማይተካ ሚና ተጫውተዋል።

ይህንን ታሪካዊ ባለውለታነት ለመዘከርና ለአትሌቶቹ የሚገባውን ክብር ለመስጠት ታስቦ የተገነባው ‘አዲስ ስፖርት ፓርክ’ በአዲስ አበባ በይፋ ተመርቋል።

አትሌቶቻችን ከሩጫ ድል ባለፈ የኢትዮጵያ "ለስላሳ ኃይል" (Soft Power) ተምሳሌቶች ናቸው። በአውሮፓውያኑ 1960 ሻምበል አበበ ቢቂላ በሮም አደባባይ በባዶ እግሩ በመሮጥ ወርቅ ሲያጠልቅ፣ ድሉ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝብ ኩራትና የአፍሪካ የነፃነት መንፈስ ነፀብራቅ ነበር።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አትሌቶቻችን የሀገራችንን የጥንታዊነት፣ የጽናትና የአሸናፊነት ታሪክ ለዓለም ሲያስተዋውቁ ቆይተዋል።

ትላንት የተመረቀው ‘አዲስ ስፖርት ፓርክ’ እነዚህን ጀግኖች በሀውልት በመዘከር፣ ታሪካቸው ለወጣቱ ትውልድ መነሳሳት እንዲሆንና ለሀገር ጎብኚዎችም የኢትዮጵያን የስፖርት ልዕልና እንዲመሰክሩ ታስቦ የተዘጋጀ የክብር ስፍራ ነው።

በኦሎምፒክ መድረክ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው በማውለብለብ እና 24 የወርቅ ሜዳሊያ በማስመዝገብ የአገራቸውን ስም በዓለም መድረክ ያስጠሩ 15ቱ ናቸው፡፡

ሻምበል አበበ ቢቂላ፦ ኢትዮጵያና የአፍሪካ የኦሎምፒክ ታሪክ ሲነሳ ቀዳሚው ኮከብ አትሌት አበበ ቢቂላ ነው። እ.ኤ.አ. በ1960 በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ በመሮጥ የማራቶን ድልን የተቀዳጀ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ ነው። በ1964 በቶኪዮ ኦሎምፒክም የራሱን ክብረ ወሰን በማሻሻል ለ2ኛ ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያ ለሀገሩ አስገኝቷል፡፡

ሻምበል ማሞ ወልዴ፦ ሻምበል አበበ ቢቂላን በመተካት በ1968 በሜክስኮ ኦሎምፒክ በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ አስገኝቷል። አትሌት ማሞ ወልዴ በዚሁ ኦሎምፒክ በ10,000 ሜትር የብር ሜዳሊያ ማግኘቱም ይታወሳል።

ሻለቃ ምሩፅ ይፍጠር፦ ማርቀያሪው በሚል ቅፅል ስሙ የሚታወቀው አትሌት ምሩፅ፣ በ1980 በሞስኮ ኦሎምፒክ በ5,000 ሜትር እና በ10,000 ሜትር ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በአንድ ኦሎምፒክ መድረክ በማሸነፍ ታሪክ ሰርቷል።

ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ፦ አትሌት ደራርቱ ቱሉ በ1992 በባርሴሎና ኦሎምፒክ በ10,000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት የመጀመሪያዋ ጥቁር አፍሪካዊት ሴት አትሌት ሆናለች። በ2000 በሲድኒ ኦሎምፒክም በዚሁ ርቀት ሁለተኛ የወርቅ ሜዳሊያዋን አሳክታለች።

ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ፦ በዓለም አትሌቲክስ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ አትሌቶች አንዱ የሆነው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ፣ በ1996 በአትላንታ እና በ2000 በሲድኒ ኦሎምፒክ በ10,000 ሜትር ለኢትዮጵያ ተከታታይ 2 የወርቅ ሜዳሊያዎችን አስገኝቷል።

አትሌት ፋጡማ ሮባ፦ አትሌት ፋጡማ ሮባ በ1996 በአትላንታ ኦሎምፒክ በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ በማሸነፍ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት የማራቶን አሸናፊ ሆና ታሪክ ፅፋለች።

አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፦ አትሌት ቀነኒሳ በኦሎምፒክ መድረክ ለኢትዮጵያ 3 የወርቅ ሜዳሊያዎች አስገኝቷል። በ2004 በአቴንስ በ10,000 ሜትር፣ እንዲሁም በ2008 በቤጂንግ በ5,000 እና በ10,000 ሜትር ድርብ ድል በማስመዝገብ የዓለምን ምርጥ አትሌት መሆኑን አስመስሯል፡፡

 አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ፦ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በኦሎምክ መድረክ 3 የወርቅ ሜዳሊያዎችን አሸንፋለች። በ2008 ቤጂንግ (5,000ሜ እና 10,000ሜ) እና በ2012 በለንደን (10,000ሜ) የወርቅ ሜድልያ ባለቤት ናት።

አትሌት መሰረት ደፋር፦ አትሌት መሰረት ጀፋር በ5,000 ሜትር ርቀት በሁለት ኦሎምፒኮች ማለትም በ2004 በአቴንስ እና በ2012 በለንደን የወርቅ ሜዳሊያዎችን ለኢትዮጵያ አስገኝታለች።

አትሌት ገዛኸኝ አበራ፦ በ2000 የሲድኒ ኦሎምፒክ በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘው ገዛኸኝ፣ ከኦሎምፒክ ድሉ በኋላ በዓለም ሻምፒዮናም በማሸነፍ በታሪክ የመጀመሪያው አትሌት ሆኖ ተመዝግቧል።

አትሌት ሚሊዮን ወልዴ፦ በ2000 የሲድኒ ኦሎምፒክ በ5,000 ሜትር ወጣት ሆኖ በመወዳደር አስደናቂ ድል በማስመዝገብ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሆኗል።

አትሌት ቲኪ ገላና፦ በ2012 የለንደን ኦሎምፒክ በማራቶን የኦሎምፒክ ክብረ ወሰንን በመስበር የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ አስገኝታለች።

አትሌት አልማዝ አያና፦ በ2016 የሪዮ ኦሎምፒክ በ10,000 ሜትር ርቀት የዓለምን ክብረ ወሰን በመስበር እጅግ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ የወርቅ ሜዳሊያ አሸንፋለች።

አትሌት ሰለሞን ባረጋ፦ በ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ (በ2021 በተካሄደው) በ10,000 ሜትር ርቀት ጠንካራ ተፎካካሪዎቹን በማሸነፍ ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝቷል።

አትሌት ታምራት ቶላ፦ የ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ፣ በአስቸጋሪው የማራቶን መስመር ላይ የኦሎምፒክ ክብረ ወሰንን በመስበር የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘቱ የኢትዮጵያን የማራቶን የበላይነት በድጋሚ አረጋግጧል።

 

በላሉ ኢታላ