ታላቋ ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ የሺህ ዘመናት ገናና ታሪክ ያላት፣ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት እና የሥልጣኔ አኩሪ አሻራን በዓለም ድርሳናት ላይ ያኖረች ሀገር ናት።
ታሪካዊቷ ኢትዮጵያ የሚያስደንቀውን ብሩህ ሥልጣኔ በመገንባት የዓለም የንግድ እና የፖለቲካ ማዕከል መሆን የቻለችው ከቀይ ባሕር ጋር በነበራት ጥብቅ፣ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ ቁርኝት ጭምር ነበር።
የባሕር በር ለኢትዮጵያ የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን የሕልውና፣ የትንፋሽ እና የታላቅነት መሠረት ነው።
ይሁን እንጂ፣ ኢትዮጵያ ይህንን የታሪክ ስብራት ለመጠገን፣ የፍትሕ እና የሐቅ ጥያቄ የሆነውን የባሕር በር አጀንዳ በጽናት ባነሣችበት በዚህ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ፣ አንዳንዶች የውስጥ ባንዳ እና የውጭ ባዳዎች በጋራ ሆነው የሀገራችንን ትኩረት ለመበተን ሌት ተቀን እየሠሩ ይገኛሉ።
ዓላማቸው ግልጽ ነው - ኢትዮጵያ ዐይኗን ከቀይ ባሕር ላይ እንድትነቅል ማድረግ። ይህንን እኩይ ዓላማቸውን ከዳር ለማድረስም በውስጣችን ግጭቶችን ይፈለፍላሉ፤ እርስ በርስ እንድንጠራጠር የዘር እና የጎሳ አጀንዳዎችን ይፈበርካሉ፤ በየዕለቱ አዳዲስ የትርምስ ወሬዎችን በመንዛት የሕዝባችንን የዕይታ አድማስ ወደ ጠባብ የሰፈር አጀንዳ ለማውረድ ይሠራሉ።
ይህ ስልታዊ የትኩረት ማስቀየስ እና መበተን ዘመቻ፣ የኢትዮጵያን ትልቁን የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳ ለማኮላሸት የተቀነባበረ ዋነኛ ስልት ነው።
ታሪክ እንደሚነግረን፣ ከዋና ብሔራዊ አጀንዳቸው ውጭ በሆኑ የውስጥ ትርምሶች ተጠምደው የጂኦ-ፖለቲካዊ ጥቅማቸውን ያስረከቡ፣ እንዲሁም ፈተናውን በፅናት ተሻግረው ታላቅነታቸውን ያረጋገጡ ሀገራት ተሞክሮ ዛሬ ለእኛ ትልቅ ትምህርት ነው።
የተሞክሮዎች ትምህርት
- የቻይና ተሞክሮ፦ በአዎንታዊው ጎን ከምንማርባቸው ሀገራት አንዷ ቻይና ናት። ቻይና በ19ኛው እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ "የውርደት ዘመን" (Century of Humiliation) በሚባለው ጊዜ ውስጥ አልፋለች። የውስጥ አርበኞች (Warlords) እርስ በርስ ሲዋጉ፣ የውጭ ኃይሎች የቻይናን ወደቦች እና የባሕር በሮች ተቆጣጥረው ነበር። ነገር ግን ቻይናውያን ከውስጥ ሽኩቻቸው ነቅተው፣ ብሔራዊ ጥቅማቸውን እና ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር በአንድነት በመቆማቸው፣ ዛሬ የዓለምን ኢኮኖሚ እና የባሕር ንግድ የሚቆጣጠር ልዕለ-ኃያል ሀገር መገንባት ችለዋል።
- የውድቀት ትምህርቶች፦ በሌላ በኩል ደግሞ፣ የትኩረት ማጣት እና የውስጥ መከፋፈል ያመጣውን ውድቀት ከሚያሳዩ ሀገራት ትምህርት ልንወስድ ይገባል። ሶማሊያ በአፍሪካ ረጅሙን የባሕር ዳርቻ (ከ3,000 ኪ.ሜ በላይ) ያላት ሀገር ብትሆንም፣ ዜጎቿ ከትልቁ ብሔራዊ የሀገር ግንባታ እና የባሕር ኃይል ባለቤትነት ራዕያቸው ይልቅ፣ በጠባብ የጎሣ ፖለቲካ እና በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት በመጠመዳቸው፣ ሀገሪቱ ለዓመታት የፈረሰች (Failed State) እንድትሆን ሆኗል። በተመሳሳይ፣ ዩጎዝላቪያ በአንድ ወቅት በአውሮፓ ጠንካራ ብሔራዊ ስሜት እና የጂኦ-ፖለቲካዊ ተጽዕኖ የነበራት ሀገር ነበረች። ነገር ግን ሕዝቦቿ በውጭ ኃይሎች አነሳሽነት በብሔርተኝነት፣ በሃይማኖትና በውስጥ ግጭቶች ሲጠመዱ፣ ታላቁን ብሔራዊ ጥቅማቸውን ዘነጉ፤ ውጤቱም ሀገሪቱ ተበታትና ወደ ትናንሽ፣ ደካማና የውጭ ጥገኛ ሀገራትነት እንድትሸነሸን አደረጋት።
እነዚህ ተሞክሮዎች የሚያስተምሩን አንድ ትልቅ ሐቅ አለ፤ ዙሪያችንን የሚጮኸው የጠላቶቻችን ድምጽ፣ እኛን እንደ ሶማሊያ ወይም ዩጎዝላቪያ ለማድረግ፣ ከዋናው የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳችን አውጥቶ በውስጥ ትርምስ ለማስጠመድ ነው። ሆነም ቀረ ግን፣ እኛ ኢትዮጵያውያን የጠላቶቻችንን ስልት ቀድመን መንቃት አለብን። ዙሪያችንን የሚጮኸውን የክፋት ድምጽ እና ትኩረት የማሳጣት ዘመቻን በመናቅ፣ ትኩረታችንን ከቀይ ባሕር ላይ ሳንነጥቅ፣ በባሕር በር አጀንዳችን ላይ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነን በአንድነት ልንቆም ይገባል።
የትውልድ አደራ
የባሕር በር ጥያቄ የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ፣ የብሔር ወይም የሃይማኖት ጥያቄ አይደለም፤ ይህ የትውልድ ጥያቄ ነው! የታሪክ ስብራትን የመጠገን ጥያቄ ነው! የፍትሕና የኢትዮጵያ ሕልውና ጥያቄ ነው! በመሆኑም፣ በውስጥ ጉዳዮቻችን ላይ ያሉንን ልዩነቶች በውይይትና በመቻቻል እየፈታን፣ በብሔራዊ ጥቅማችን ላይ ግን ብረትን የሚያቀልጥ አንድነት ሊኖረን ግድ ይላል።
የነገዋ ብሩህ ኢትዮጵያ የምትገነባው፣ ዛሬ በሚነዙ የትርምስ ወሬዎች ተሰርቀን ራዕያችንን ወደ ጎን ስንተው ሳይሆን፣ ከማዕበሉ በላይ ከፍ ብለን የነገውን ብልጽግናችንን አሻግረን ስናይ ነው። ዛሬም፣ ነገም፣ ሁሌም፣ በጽናት እንላለን - ዐይናችንን ከቀይ ባሕር አንነቅልም! የትውልዱን አደራ፣ የሀገርን ክብር እናስመልሳለን!
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ