Search

ለምንድነው ወደ “አረንጓዴ ጉዞ” መሸጋገር የግድ የሚለን? የነገዋን ከተማ ዛሬ የመገንቢያ ቁልፍ

ማክሰኞ መጋቢት 29, 2018 116

በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከሰተ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም እና የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ አረንጓዴ የትራንስፖርት አማራጮች አሁን ላይ ዋነኛ መፍትሔ ሆነው ቀርበዋል።
በከተሞቻችን የሚታየውን የአየር ብክለት ለማስወገድ ከነዳጅ ተሽከርካሪዎች ወደ ንጹህ ኢነርጂ የሚደረገው ሽግግር የሚጫወተው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው።
አረንጓዴ ትራንስፖርት ስንል የአካባቢ ብክለትን፣ የኃይል ብክነትን እና በነዳጅ ላይ ያለን ጥገኝነትን ለመቀነስ ታስበው የተዘጋጁ የጉዞ አማራጮችን የሚያካትት ዘላቂ ሥርዓት ነው።
በአሁኑ ወቅት አውሮፓ ኅብረት እስከ 2050 የካርቦን ልቀትን ዜሮ ለማድረስ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እያደረጉ ሲሆን፣ ቻይና ደግሞ በኤሌክትሪክ መኪና አምራችነት ዓለምን እየመራች ትገኛለች።
እንደ አምስተርዳም እና ፓሪስ ያሉ ከተሞችም ብስክሌት እና የእግር ጉዞን ዋነኛ አማራጭ በማድረግ ለሌሎች ተምሳሌት ሆነዋል።
በኢትዮጵያ በተለይ በአዲስ አበባ ይህን ተሞክሮ ለመተግበር የሚያስችሉ ሰፋፊ መሰረተ ለማት ግንባታዎች እና ማበረታቻዎች ቀርበዋል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን፣ የጋራ ትራንስፖርትን እና ሞተር አልባ ጉዞዎችን በማስፋፋት ጤናማ እና ንጹህ ከተማን መፍጠር ይቻላል።
የአረንጓዴ ጉዞ ጥቅሞች ዘርፈ ብዙ ናቸው፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ከነዳጅ እጅግ ርካሽ በመሆኑና የጥገና ወጪን በመቀነሱ ለኪስ ተስማሚ ነው።
ከዚህም ባለፈ የኤሌክትሪክ መኪናዎች ከነዳጅ መኪናዎች በበለጠ ከ85 በመቶ በላይ ኃይልን ወደ እንቅስቃሴ የመቀየር ብቃት ስላላቸው ለኢነርጂ ቁጠባ አይነተኛ ድርሻ አላቸው።
የእግር ጉዞንና የብስክሌት አጠቃቀምን በማሳደግ የተሻለ ጤናን መፍጠር የሚቻለው፣ ከጭስና ከብክለት የጸዳው አረንጓዴ ትራንስፖርት ለከተሞቻችን ያለውን አይተኬ ሚና በተግባር ማዋል ሲቻል ብቻ ነው።
በቢታኒያ ሲሳይ