ለአየር ንብረት ለውጥ የማትበገር አፍሪካን ለመገንባት አህጉራዊ አንድነታችን ወሳኝ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በሰው ልጅ መገኛዋ ኢትዮጵያ፣ በአፍሪካውያን መሰባሰቢያ አዲስ አበባ፣ 16ኛውን የአፍሪካ የሥጋት መከላከል ዐቅም ጉባኤ (ARC-COP16) በይፋ አስጀምረዋል።
አህጉራችን በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ እየተፈተነች ትገኛለች ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሆኖም ይህ ፈተና ተስፋችንን የሚያጨልም፣ ጉዟችንን የሚገታ አይሆንም ብለዋል። አጋጣሚው በእልህ፣ በቁጭትና በእንችላለን ኅብረት አንድነታችንን የምናጠናክርበት መሆኑንም ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በመልዕክታቸው እኛ አፍሪካውያን ከአደጋ በኋላ ለሚመጣ ርዳታ እጅ ከመዘርጋት ይልቅ፣ አደጋን ቀድሞ መከላከልና በሳይንሳዊ መንገድ ለመፍትሔ መዘጋጀት የህልውናችን መሠረት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ራዕይ ሰንቃ፣ ክንዷን አበርትታ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ዐቅም እየገነባች መሆኗን ገልጸዋል። በአረንጓዴ ዐሻራ የምድርን ገጽታ እየቀየርን ነው፤ በምግብ ሉዓላዊነት ንቅናቄ ራሳችንን ለመቻል እየተጋን ነው፤ በታዳሽ ኃይል ልማትም የአህጉራዊ ትሥሥር ገመድ እየሆንን ነው ሲሉም አክለዋል።
ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በበዙበት፣ በአንጻሩ ዓለም አቀፋዊ ድጋፎች በቀነሱበት በዚህ ወቅት፣ የአፍሪካ ሥጋትን የመከላከል ዐቅም (African Risk Capacity-ARC) የመሰሉ አህጉራዊ ተቋሞቻችንን ማጠናከር አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በመጨረሻም የአደጋ ሥጋትን በጥናት መለየት፣ ቀድሞ መከላከል፣ ችግር ሲከሠትም በአፍሪካዊ ዐቅም ምላሽ መስጠት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያም ለዚህ የአፍሪካውያን ሌላኛው የሉዓላዊነት ግብ መሳካት በአርአያነት እንደምትተጋ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አረጋግጠዋል።