Search

የፀሎተ ሐሙስ ሰባቱ ስያሜዎች እና የቤተክርስቲያን ሥርዓቶች

ሓሙስ ሚያዝያ 01, 2018 128

ፀሎተ ሐሙስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከሰሞነ ሕማማት ቀናት አንዱ ሲሆን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ድኅነት ሲል የተቀበላቸውን መከራዎችና የፈጸማቸውን መንፈሳዊ ድርጊቶች የምናስብበት ዕለት ነው።
ይህ ዕለት በቤተክርስቲያን ትውፊትና በአባቶች ትምህርት መሠረት የተለያዩ ስያሜዎችና ጥልቅ ምሥጢራት አሉት። ሰባት የተለያዩ ትርጓሜዎችንም ይዟል፡፡
የመጀመሪያው "ፀሎተ ሐሙስ" የሚለው ሲሆን፣ የስያሜው ትርጓሜ ኢየሱስ ክርስቶስ በጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ እስከ መያዙ ድረስ ሲጸልይ በማደሩ የተሰጠ ነው።
የፀሎተ ሐሙስ ሌላኛው ስያሜ እግር የማጠብ የሚከናወንበት ዕለት በመሆኑ የ"ሕፅበት ሐሙስ" ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ፍጹም ትሕትናን ያስተማረበት ዕለት ነው።
በዚህ ዕለት ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የመጨረሻውን እራት የተመገበበት ዕለት በመሆኑ ደግሞ ዕለቱ "ምሴተ ሐሙስ" ተብሎም ይጠራል “ምሴት" ማለት እራት ማለት ነው።
ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን አንዱ የሆነው ምሥጢረ ቍርባን የተመሠረተበት ዕለት በመሆኑ ደግሞ ፀሎተ ሐሙስ "የምሥጢር ቀን" ይባላል።
እንደ ቤተክርስቲያን አባቶች አስተምህሮ ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ለሰው ልጆች የዘላለም ቃል ኪዳን የገባበትና የመሥዋዕተ ኦሪት ማብቂያ መሆኑ የታወጀበት ዕለት በመሆኑ ዕለቱ "የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ" ተብሎም ይጠራል።
የሰው ልጅ ከኃጢአትና ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ የወጣበት፣ የጠፋው ክብር የተመለሰበት ዕለት በመሆኑ "የነፃነት ሐሙስ" የሚል ስያሜ እንደተሰጠም የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ያስተምራሉ፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ በአትክልት ሥፍራ (በለመለመ ቦታ) ስለጸለየ የተሰጠው ስያሜ ደግሞ "አረንጓዴው ሐሙስ" የሚል ነው፡፡
በዕለቱ ጳጳሳት ወይም ካህናት የኢየሱስ ክርስቶስን ትሕትና አርአያ በማድረግ የምእመናንን እግር ያጥባሉ፤ ለዚህ ሥርዓትም የወይራና የወይን ቅጠሎች ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡
በዕለቱ ከባቄላ፣ ከስንዴ ወይም ከገብስ የሚዘጋጅ "ጉልባን" የተባለ ንፍሮ ይበላል። ይህ ምግብ እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ሲወጡ ያልቦካ ቂጣና ንፍሮ ይዘው መውጣታቸውን ለማስታወስ የሚዘጋጅ ነው።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ