Search

የአዋሽ ወንዝ በየዓመቱ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ዘላቂ የመፍትሄ ስራ ይከናወናል - አቶ አወሉ አብዲ

Aug 11, 2025

የአዋሽ ወንዝ ተፋሰስ በየዓመቱ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ዘላቂ የመፍትሄ ስራ በቀጣይ እንደሚከናወን የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አወሉ አብዲ ተናገሩ።

አቶ አወሉ አብዲ በአዋሽ ወንዝ መሙላት ምክንያት ከቤታቸው ተፈናቅለው በትምህርት ቤቶች ተጠልለው የሚገኙ ዜጎችን ተዟዙረው ጎብኝተዋል።

በአዋሽ ወንዝ መሙላት ምክንያት በተፈጠረ ጎርፍ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን 5 ወረዳዎች የሚገኙ 20 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ተፈናቅለዋል።

ተፈናቃዮቹ በዞኑ ኢሉ ወረዳ ተፍኪ እና ተጂ አካባቢዎች በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በጊዜያዊ ማረፊያ ተጠልለው ይገኛሉ።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አወሉ አብዲ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ጌቱ ገመቹ በጊዜያዊ መጠለያዎች ተገኝተው ተፈናቃዮችን አነጋግረዋል።

በክልሉ ቡሳ ጎኖፋ አማካኝነት የተለያዩ የዕለት መሰረታዊ ፍጆታዎች ለተፈናቃዮች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አቶ አወሉ ተናግረዋል።

በክልል ደረጃ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ ይገኛል ብለዋል።

አቶ አወሉ እንደገለፁት የክልሉ መንግስት ጀልባዎችን በፍጥነት በማሰባሰብ የሰው  እና የእንስሳት ህይወት ሳይጠፋ ተጎጂዎችን ከአካባቢው ማውጣት ተችሏል።

በቡሳ ጎኖፋ አማካኝነት የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው መደረጉንም ገልጸዋል።

የአዋሽ ወንዝ ተፋሰስ በየዓመቱ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ዘላቂ የመፍትሄ ስራ በቀጣይ እንደሚከናወን አቶ አወሉ ተናግረዋል።

ክልሉ የሚከሰቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመከላከል የሚያስችል ዝግጁነት እንዳለው የጠቀሱት አቶ አወሉ፤ ለተፈናቃዮች ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ አካላትም በቡሳ ጎኖፋ በኩል ድጋፍ ማድረግ የሚችሉ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።

በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች በበኩላቸው፤ በመንግስት እየተደረገላቸው ያሉ ድጋፎችን አመስግነው፤ ድጋፉ መጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል።

በሞላ ዓለማየሁ

#EBC #ebcdotstream #flood #Awash