የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ የ2018 ዓ/ም የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤን በዓል በማስመልከት ለመላው ምዕመናን ያስተላለፉት መልዕክት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
“ሰዎች ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ”(1ቆሮ.15፡22)
በክርስቶስ የተወደዳችሁ ብፁዓን ጳጳሳት፤ ክቡራን ካህናት፤ ገዳማውያንና/ውያት መላው ሕዝበ ክርስቲያንና የአገራችን ህዝቦች፤ በመላው ዓለም የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወገኖች፤
እንኳን ለ2018 ዓ/ም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ።
ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚለው “እነሆ ሞት በድል ተዋጠ” (1ኛ ቆሮ.15፡54)
ምድር በክርስቶ ደም ታጥባ በክርስቶስ ፋሲካ ተደሰተች፤ የምድር ልጆች ከሁሉ የሚበልጠው የምሥራች ተበሠረላቸው፡፡ ደስታና ፍቅር፤ ብርሃንና ሰላም ለሁሉም ህዝቦች ተዳረሰ፡፡ እኛም ይህንን የክርስትናችን መሠረት የሆነውን በዓል በአግባቡ የምናከብረው የክርስቶስን ተልዕኮ በአግባቡ በተረዳነው መጠን ነው፡፡
ወንጌልን በማስተዋል ስናነብና ስናሰላስል በክርስቶስ በኩል የሚገለጠውን የእግዚአብሔርን ሥራ እንመለከታለን፡፡ መጀመሪያ የመንግስቱ ስጦታና የምሥራች፤ ከዚያም የንሰሐ ጥሪ እነሆ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር የተስፋ ከተማ የእስራኤልና የአሕዛብ መከማቻ እንደሲና ተራራ የመገናኛ ቦታ በሆነው ቤተመቅደስ በሚገኝበት በኢየሩሳሌም ይገኛል፡፡ ከዚህ ከተማ ወንጌልና የክርስቶስ ትንሣኤ እስከ ዓለም ዳርቻ ይሰበካል፡፡
በመፅሐፍ ቅዱስ እንደምናየው እግዚአብሔር ከሁሉ አስቀድሞ የተግባርና የተመክሮ አምላክ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ተመክሮ ደግሞ በልጁ ሥጋ መልበስ ፍፁምነትን አግኝቷል፡፡ የክርስቶስ የትንሳኤው ምስጢር አንድን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የመላውን የሰው ልጅ ሕይወትን እንደሚመለከት የምንረዳው በወንጌልና በትንሣኤ የምሥራች ነው፡፡ ስቃይና ክብር፤ ሞትና ትንሣኤ፤ ድካምና ኃይል በወንጌል ፍጻሜን ሲያገኙ የምናየው በጌታችን ኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ነው፡፡
ክርስቶስ ስለማንነቱ ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል? እና እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ? (ማቴ.16፡13-15) ብሎ ከጠየቃቸው ጊዜ ጀምሮ ደቀመዛሙርቱ በጥርጣሬና በግራ መጋባት ውስጥ ነበሩ፡፡ ለመመለስ ድምፁን ከፍ አድርጎ የተናገረው ጴጥሮስ ብቻ ነበር ነገር ግን የሕማማቱ መታወጅ አሳዘናቸው፡፡ ኢየሱስ አሰቃቂ ሞት እንዳይደርስበት ተመኙ፡፡ የመምህራቸውን መከራ እንዴት ሊቀበሉት ይችላሉ? ኢየሱስን መለየት ከባድ ሊሆን ቢችልም እስከ ኢየሩሳሌም መከተል ግን ይበልጥ ከባድ ነበር፡፡ ሆኖም ግን የራሱን ፈቃድ ትቶ የእርሱን ፈቃድ ለመፈለግ ተጉ፡፡
መስቀልን ተሸክሞ በመከተልና ያለመስቀል ለመከተል በመሞከር መካከል መሠረታዊ ልዩነት አለ፡፡ ሰው ከመስቀልና ከመሞት ወደ ትንሣኤ ይሻገራል፡፡ ያለመስቀል እርሱን ለመከተል መሞከር ለኢየሱስ ብቁ አለመሆን ነው፡፡ ይህም ሳይሞቱ ለመኖርና ለመነሣት መፈለግ ነው፡፡ ምንም ዓይነት አቋራጭ መንገድ የለም፡፡ ወደ እርሱ በድረስ የምንችለው በመስቀል በኩል ብቻ ነውና፡፡ ክርስቶስን ስናዳምጠው ልክ እንደ ኤማሁስ ደቀመዛሙርት ልባችን ይቃጠላል፡፡ በልግስና በመካፈል ስንኖር ዓይኖቻችን ይበራሉ፡፡ አዲሱ እረኛ ክርስቶስ በሕይወት ምድረበዳ ሁሉ ይመራናል ይጠብቀናል ይመግበናል፡፡ እንደ ኤማሁስ ደቀመዛሙርት በፈተናዎች ውስጥ ልናልፍ እንችላለን፡፡ ነገር ግን በሕማማቱ ላይ ብቻ አንቆምም፡፡ የመንፈሳዊ ሕይወት በግል ፍጻሜ መጽናኛና ሕብረት ይሆነናል፡፡ እኛም እንደ መጀመሪያዎቹ የጌታ ደቀመዛሙርት በሞቱና በትንሣኤው እንካፈላለን፡፡
በየዓመቱ የምናከብረው የትንሣኤ በግል የጌታ ቀን፤ የድል ቀን በማለት እንጠራዋለን፡፡ በዓሉንም ስናከብር የጌታን ትንሣኤ ምስጢር ለመረዳት፤ ለመሳተፍ እና ለመኖር ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የትንሣኤ በዓል የክርስቲያኖች የትንሣኤ ቀን ነው፡፡ ምክንያቱም የሃይማኖታችን መሠረት ነውና፡፡
በዚህ ቀን ብዙ ነገሮች ተከናውነዋል፡፡ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ሃጢያትና ሞት ድል ተነስተዋል፡፡ የመጀመሪያው አሮጌው በኃጢያት የተበከለው ፍጥረት ፍጻሜውን አግኝቶ አዲስ ፍጥረት በክርስቶስ ተጀምሯል (2ቆሮ 5፤17) እኛም በዚህ በፋሲካ ቀን አዲሱን የዓለም የመጀመሪያ ቀን እናስታውሳለን፡፡ የመጨረሻውንም ቀን በተስፋ እንጠባበቃለን፡፡ ይኸውም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር የሚመጣበት ቀን ነው ፡፡(የሐ.ሥራ1፤11)
የክርስቶስ ትንሣኤ የክርስትና እምነት መሠረት የተጣለበት ሂደት ነው፡፡ (1ቆሮ 15፤14) የዚህ ሂደት ታሪካዊ ገጽታው የተነሣውን ክርስቶስን ለማየት በታደሉ ሰዎች ተመስክሯል፡፡ እንዲሁም በእምነት ብርሃን ለሚቀበሉትም አስደናቂ እውነታ ነው፡፡
ይህ ክስተት በሰው ልጆች ታሪክ ልዩ ከመሆኑም ባሻገር የጊዜንም ጥልቅ ምስጢር በውስጡ የያዘ ነው። ጊዜ ሁሉ የክርስቶስ ነው፤ ዘመናትም ሁሉ የእርሱ ናቸው፤ በእርሱ ዕቅድ መሠረት ፍጥረት ሁሉ ወደ ታቀደለት ዓላማ በመገስገስ ላይ ነው፡፡ ይህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመሠረተው የክርስቲያኖች ቀን የደስታና የተስፋ ቀን ነው፡፡
የተወደዳችሁም ምዕመናን፤
ትንሣኤን የሚያምኑ ልጆች እንደመሆናችን መጠን ሕይወታችን ደስታንና ተስፋን ያዘለ እንዲሆን ተጠርተናል፡፡ በምናደርገው በሕይወታችን ሁሉ የአምላክ ቃል መቃኛችን ሊሆን ይገባል፡፡ የአምላክን ቃል የሚቋቋም ቅዱስ መንፈሱን የሚያሳዝን ከክርስትና ሕይወት ያልተስማማ ጥላቻን፤ መለያየትንና መገዳደልን ሁሉ እናስወግድ፡፡ በእውነት ፈጣሪያችንንም እንደምንወድ በቃላችንና በስራችን እናሳይ፡፡ በቤታችንም ሆነ በአገራችን የሚገዛን ጌታ አድርገን እንሹመው፡፡ ወደርሱ በመቅረብ በጽድቅ ሕይወት በመጽናት፤ በህይወታችን መልካም ምግባርን እናሳይ፡፡ ከመላው የአገራችን ህዝቦች ጋር በመተባበርና በአንድነት እንቁም፡፡ በቅንነት በመቆም መጥፎ ስራን እንቃወመው፡፡ ሁላችንም ስለ ሰዎች ሕይወት ግድ ይበለን፡፡ እርስበርሳችንም ይቅር በመባባል ትንሣኤያችንን እናክብረው፡፡
እኛም ካቶሊካውያን ምዕመናን ይህንን በዓል ስናከብር እንደተለመደው ከችግረኞች፤ አስታዋሽ ከሌላቸው፤ በጎዳናና በየመጠለያ ቦታዎች ላይ ያሉ ወገኖቻችንን በማገዝና በመርዳት እንድናከብር አደራ ማለት እንወዳለን፡፡
መጪውን 7ኛውን የአገራችን የኢትዮጵያ ሕዝብ ምርጫ በሰላምና በመግባባት ተከናውኖ እንዲፈጸም ሁላችንም እንድንተባበር እንድንፀልይ አደራ እንላለን፡፡
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዎ 14ኛ ለሁላችንም በመጪው ቀዳም ስዑር በሀገራችን በፋሲካ ዋዜማ ስለአለም ሰላም ሁሉ እንድንጸልይ አደራ ብለዋልና ሁላችንም በዚያ ቀን ለአለም ሰላም ከእሳቸው ጋር እንድንጸልይ አደራ እላለሁ።
በመጨረሻ፣ በዓለ ትንሣኤው በአገራችን የተፈጥሮ ጉዳት ላጋጠማቸው መፅናናትን፤ በአገራችንና በመካከለኛው ምስራቅ ባሉት አገሮች የሚካሄዱትን ጦርነቶች እንዲቆሙና ሰላም እንዲወርድ፤ ለታመሙት ምህረትን፤ ላዘኑት መጽናናትን፤ በችግርና በጭንቀት ላይ ላሉ በጌታ መጎብኘትን፤ ለታሰሩት መፈታትን፤ ለተፈናቀሉ ወደ ቀያቸው መመለስን፤ ለተራቡና ለተጠሙ ምግብና ውሃን እንዲሰጥልን፤ የተራራቁትን እንዲያቀራርብልን በአጠቃላይ የትንሣኤው ፍሬ ፍቅርንና ወዳጅነትን፤ ትዕግስትና ትሕትናን የምናሳይበት ያድርግልን፡፡
መልካም የትንሣኤ በዓል!
ልዑል እግዚአብሔር አገራችንን ይባርክልን ይጠብቅልን
+ ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ
ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት