Search

ትንሣኤ፦ የሰው ልጅ ከሞት ወደ ሕይወት የተሻገረበት "የዕርቅና የመዳን ዕለት"

እሑድ ሚያዝያ 04, 2018 305

በክርስትና እምነት ተከታዮች፣ በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ፣ ትንሣኤ (ፋሲካ) የሃይማኖቱ መሠረት እና ከዐበይት የኢየሱስ ክርስቶስ በዓላት መካከል ቀዳሚው ተደርጎ ይወሰዳል። "ፋሲካ" የሚለው ቃል "ፓስካ" (Pascha) ከሚለው የእብራይስጥ ቃል የመጣ ሲሆን፣ ትርጉሙም "ማለፍ" ወይም "መሻገር" ማለት ነው።

ትንሣኤ በምዕመናን ዘንድ እንዴት ይታሰባል?

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የበዓሉ ዝግጅት የሚጀምረው ከ55 ቀናት በፊት ነው። "ሁዳዴ" ወይም "ዐቢይ ጾም" ተብሎ በሚጠራው በዚህ ወቅት፣ ምዕመናን ከማንኛውም የእንስሳት ተዋጽኦ በመከልከል፣ በጸሎት እና በስግደት ክርስቶስ የጾመውን ጾም እያሰቡ ይቆያሉ።

በተለይም ከሆሳዕና ዕለት ጀምሮ ያለው ሳምንት፣ "ሰሙነ ሕማማት" በመባል የክርስቶስ መከራ የሚታሰብበት በመሆኑ፣ ምዕመናን በቤተክርስቲያን በመገኘት ከፍተኛ መንፈሳዊ ተጋድሎ እና ስግደት ያከናውናሉ። የትንሣኤ ዕለት (ቅዳሜ ሌሊት) በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የሚከናወነው የማኅሌት እና ቅዳሴ ሥርዓት የበዓሉ ከፍተኛ መገለጫ ሲሆን፣ ምዕመናን ነጭ የሀገር ባህል ልብስ ለብሰው እና ጧፍ አብርተው የትንሣኤውን ብሥራት በደስታ ይጠባበቃሉ።

አቅም የፈቀደላቸው ምዕመናን ከሐሙስ ዕለት ምሽት፣ ያልቻሉት ደግሞ ከዓርብ ምሽት ጀምረው እህል ውሃ ሳይቀምሱ በማክፈል እስከ ትንሣኤው ይቆያሉ። ተምሳሌትነቱም ክርስቶስ በተያዘ እና በተሰቀለ ጊዜ ሐዋርያት በሐዘን እና በፍርሃት ተውጠው እህል ውኃ ሳይቀምሱ እስከ ትንሣኤው መቆየታቸውን ለማመልከት ነው።

የዕርቅና የመዳን ዕለት

የቤተክርስቲያን ሊቃውንት እና አባቶች ትንሣኤን "ዕለተ ዕርቅ" እና "ዕለተ መድኃኒት" (የመዳን ዕለት) ብለው ይጠሩታል። እንደ ሃይማኖተ አበው እና የቅዱስ ያሬድ ድጓ ባሉ የቤተክርስቲያን መጻሕፍት መረጃ መሠረት፣ ትንሣኤ የሚከተሉት ጥልቅ ትርጉሞች አሉት፦

ዕለተ ዕርቅ፦ በአዳም ውድቀት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው በፈጣሪ እና በፍጡር መካከል ያለው ግንኙነት የታደሰበት፣ የጥል ግድግዳ ፈርሶ ሰላም የወረደበት ዕለት ተደርጎ ይታመናል።

ዕለተ መድኃኒት (የመዳን ቀን)፦ በሊቃውንቱ ትርጓሜ "ማዕዶት" (መሻገር) የሚለው ጽንሰ-ሐሳብ የሚገለጽበት ሲሆን፣ የሰው ልጅ ከሲኦል ወደ ገነት፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ እንዲሁም ከሞት ወደ ሕይወት መሻገሩን ያመለክታል።

የቃል ኪዳን መፈጸሚያ፦ ለአዳም እና ለልጆቹ የተገባው የመዳን ተስፋ የተፈጸመበት ዕለት መሆኑም በስፋት ይነገራል።

የትንሣኤ ሰላምታ

በበዓሉ ዕለት እና ከዚያ በኋላ ባሉት 50 ቀናት ምዕመናን ሲገናኙ የሚለዋወጡት ልዩ መንፈሳዊ ሰላምታ አላቸው። ይህ ሰላምታ በግዕዝ ቋንቋ የሚቀርብ ሲሆን፣ ጥልቅ ሃይማኖታዊ መልዕክት ያዘለ ነው፦

ሰላምታ ሰጪ፦ "ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን!" (ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ!)

ተቀባይ፦ "በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን!" (በታላቅ ኃይል እና ሥልጣን!)

ሰላምታ ሰጪ፦ "አሰሮ ለሰይጣን!" (ሰይጣንን አሰረው!)

ተቀባይ፦ "አጋዞ ለአዳም!" (አዳምን ነጻ አወጣው!)

ሰላምታ ሰጪ፦ "ሰላም!" (ሰላም!)

ተቀባይ፦ "እምይእዜሰ!" (ከዛሬ ጀምሮ!)

ሰላምታ ሰጪ፦ "ኮነ!" (ሆነ!)

ተቀባይ፦ "ፍሥሐ ወሰላም!" (ደስታና ሰላም!)

ማኅበራዊ እና ባህላዊ እሴቶች

ትንሣኤ ሃይማኖታዊ ይዘቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ እጅግ የላቀ ማኅበራዊ ፋይዳ አለው። በዓሉ ከረዥም የጾም እና ሱባዔ በኋላ የሚመጣ በመሆኑ፣ ማኅበረሰቡን በአንድነት የሚያስተሳስሩ ልዩ ልዩ ኩነቶች ይስተናገዱበታል።

ጎረቤቶች በጋራ የሚያዋጡት እና የሚያርዱት ቂርጫ፣ በጋራ የሚቋደሱት ማዕድ እንዲሁም ቤተሰብ ተሰባስቦ በጋራ የሚቆርሰው ድፎ ዳቦ የፍቅር እና የአንድነት ተምሳሌቶች ናቸው።

ከዚህም ባለፈ ትንሣኤ መንፈሳዊ "ዕለተ ዕርቅ" እንደመሆኑ መጠን፣ ይህ ምሥጢር ወደ ማኅበራዊ ሕይወት ወርዶ በሰዎች ዘንድም ይተገበራል።

የተጣሉ የሚታረቁበት፣ የታመሙና አረጋውያን የሚጠያየቁበት፣ እንዲሁም ያለው ለሌለው አካፍሎ ደስታን በጋራ የሚቋደሱበት አብሮነትን የሚያጠናክር ታላቅ ማኅበራዊ እሴት ነው።

መልካም የትንሣኤ በዓል!

በለሚ ታደሰ

#Ethiopia #Easter #EBC