የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ከውኃዎቿ እና ከባህር በሮቿ ጋር የተቆራኘ ነው። ኢትዮጵያ በታሪኳ የባህር በር በነበራት ዘመን፣ የሥልጣኔዋ ገናናነት እና ዝና ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። ታሪክ እንደሚመሰክረው፣ ሀገሪቱ ለቀይ ባህር በቀረበች ቁጥር የከፍታ ዘመኗን ስታረጋግጥ ቆይታለች።
ከ1978 እስከ 1983 ዓ.ም በአሰብ ወደብ በባህር ትራንስፖርት ባለሥልጣን ሰራተኛ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ወ/ስላሴ፣ የአሰብን ማህበራዊ ድባብ ሲያስታውሱ "አሰብ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ እና እጅግ ሀብታም ከተማ ነበረች" ይላሉ። አሰብ ሰቂር (ትንሿ አሰብ) የአፋር ተወላጆች በብዛት የሚኖሩባት ስፍራ ስትሆን፣ ከተማዋ ለማኝ የማይታይባት፣ ወጣቱ ሰርቶ የሚያድርባት እና 24 ሰዓት ንቁ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድባት ወደብ ነበረች። በወቅቱ ኢትዮጵያ በካሊብ ደሴት ላይ ጀልባዎችን ትገጣጥም፣ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካም ነበራት ይላሉ ታሪክን የኋሊት እየቀኙ።
አፋር እና አሰብ፡ ሰው ሰራሽ ድንበሮች
የቀድሞ የመከላከያ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ጸድቃን ገብረትንሳኤ እንደሚያስረዱት፣ በአፋር ህዝብ መካከል ያለው ድንበር ሰው ሰራሽ (Artificial) ነው። አፋሮች ከአጽቢ እስከ ቦዲ፣ ከራፋይሌ እስከ አሰብ ድረስ እየተንቀሳቀሱ የሚነግዱ እና የሚኖሩ እንጂ በድንበር የተገደቡ አይደሉም ይላሉ።
የቀድሞ ሰራዊት አባል ብሪጋዴር ጄነራል ገብረጊዮርግስ አስራት በበኩላቸው፣ አሰብ የኢትዮጵያ የቀይ ባህር መሬት መሆኗን ያነሳሉ። እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ ኤርትራ አሰብን አስተዳድራ አታውቅም፤ አሰብ ቀደም ሲል በወሎ ጠቅላይ ግዛት ስር፣ በኋላም አፋር ራስ ገዝ ሲሆን ራሱን ችሎ ይተዳደር የነበረ የኢትዮጵያ አካል ነው በጀግንነት ስሜት።

የባህር በር ማጣት ያስከተለው ጉዳት
ጄነራል ጸድቃን እንደሚሉት የአንድ ሀገር ብሔራዊ አቅም በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በሚሊተሪ እና በዲፕሎማሲ ተሰሚነት እንደሚለካ ይገልጻሉ። ኢትዮጵያ የባህር በር በማጣቷ እነዚህን ሀገራዊ ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ ትልቅ ዋጋ እየከፈለች ትገኛለች። "የባህር በር የምናጣው በማይገባን አይነት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ውስጥ ሆነን ነው" ይላሉ።
የ1990ው ጦርነት እና የአሰብን የማስመለስ ዕድል
በ1990 ዓ.ም ኤርትራ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት፣ ኢትዮጵያውያን ጦርነቱን በህገ-ወጥ መንገድ የተወሰደውን ወደብ ለማስመለስ እንደ መልካም አጋጣሚ ቆጥረውት ነበር። በጦርነቱ ማጠናቀቂያ ላይ የኢትዮጵያ ሰራዊት ከአሰብ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው "ባይሞከር" ስፍራ ደርሶ የነበረ ቢሆንም፣ በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ውሳኔ ምክንያት ሰራዊቱ ወደ ኋላ እንዲመለስ ተደርጓል።
ጄነራል ጸድቃን እንደሚሉት፣ ያኔ በህጋዊም ሆነ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ አሰብን ማስመለስ የሚቻልበት ሙሉ አቅምና ሽፋን የነበረ ቢሆንም፣ በኢህአዴግ ውስጥ በነበረው የፖለቲካ ሽኩቻ ምክንያት አጋጣሚው ሳይጠቀምበት ቀርቷል ይላሉ።

የአልጀርስ ስምምነት እና "የክህደት" ውሳኔዎች
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታት በአልጀርስ የተደረገው ስምምነት፣ የኢትዮጵያን ታሪካዊና ህጋዊ የባህር በር መብት ያላከበረ ነበር። መንግስት ትኩረቱን በውስጥ ስልጣን ሽኩቻ ላይ በማድረጉ፣ ሀገሪቱ ያሏትን ማስረጃዎች ተጠቅማ መብቷን ሳታስከብር ቀርታለች፣ ይህም ኢትዮጵያን ለብዙ ክሳራ ደርጎታል ይላሉ።

አዲሱ ምዕራፍ፡ የቀይ ባህር አጀንዳ
ከ2010 ዓ.ም የመጣውን ለውጥ ተከትሎ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተዳፍኖ የቆየውን የቀይ ባህር በር ጉዳይ ዳግም ወደ አደባባይ አውጥተውታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ "የኢትዮጵያ የቀይ ባህር አክሰስ ጉዳይ አይቀሬ ነው፤ ይህንን በሰላም እና በንግግር ለመፍታት አለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲሸመግሉን እንፈልጋለን" ሲሉ አቋማቸውን ገልጸዋል።

ዛሬ የባህር በር ጥያቄ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ሆኗል የሚሉት ጄነራል ጸድቃን ኢትዮጵያ "በመስጠት እና መቀበል" መርህ እንዲሁም በዲፕሎማሲያዊ ትግል ወደ ቀይ ባህር የመመለሷ ጉዳይ አሁን ላይ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል። ይህ አጀንዳ ቀደም ሲል እንደ "ታቡ" ይታይ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ግን የባህር በር ከሌለ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንደማይኖር አለም አቀፍ ግንዛቤ እየተያዘበት ይገኛል ሲሉ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሀሳባቸውን አጋርተዋል።
ኢትዮጵያ ትናንት በሴራ እና በክህደት ያጣችውን የባህር በር መብቷን በህጋዊ እና በታሪካዊ አግባብ ለማስመለስ የጀመረችው ጉዞ፣ ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ብልጽግና እና ትንሳኤ መሰረት እንደሚሆን ይታመናል።
በመሐመድ ፊጣሞ