የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ በተጀመረው የሪፎርም ሥራ እስካሁን 50 በመቶ የሚሆኑ የመንግሥት አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ በማድረግ ወደ “መሶብ” ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማስገባት መቻሉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
የአገልግሎት አሰጣጡን ተደራሽ፣ ፈጣን እና ከሙስና የጸዳ ለማድረግ ታስቦ የተጀመረው ይህ ስልታዊ እንቅስቃሴ ነዋሪዎች የንግድ ፈቃድ ማደስን፣ ግብር ማሳወቅንና የግንባታ ፈቃድ ማግኘትን የመሰሉ አገልግሎቶችን ከቤታቸው ወይም ከሥራ ቦታቸው ሆነው በኮምፒውተርና በሞባይል እንዲያከናውኑ አስችሏቸዋል።
በአራዳ ክፍለ ከተማ የተጀመረው የ“መሶብ” ዲጂታል አገልግሎት በአሁኑ ወቅት ወደ ሥድስት ማዕከላት ማደግ የቻለ ሲሆን፣ አገልግሎቱን ካገኙ 130 ሺህ ነዋሪዎች መካከል 98 በመቶ የሚሆኑት በተደረገላቸው መስተንግዶ መርካታቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይ አንድ ወር ውስጥም በቀሪዎቹ አምስት ክፍለ ከተሞች ዘመናዊ የዲጂታል አገልግሎት መስጫ ሕንጻዎች ተጠናቅቀው ወደ ሥራ ሲገቡ፣ መላው አዲስ አበባ በዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንደምትሸፈን ይጠበቃል።
በሥራ ብዛት ወደ ቢሮ መምጣት ለማይችሉ ነዋሪዎች ምቾት ሲባል ደግሞ በዘመናዊ አውቶቡሶች ላይ የተገጠሙ “ተንቀሳቃሽ የዲጂታል አገልግሎት መስጫዎች” በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምሩ ከንቲባዋ አስታውቀዋል።
ይህ የማዘመን ሥራ የተገልጋዩን ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ ከመቆጠቡ ባለፈ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለውን ትስስር እንደሚያጠናክር የተገለጸ ሲሆን፣ በቀጣይ ከሦስት እስከ አምስት ዓመታት ውስጥ አዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ በስማርት አገልግሎቶች ለማዳረስ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል።
በላሉ ኢታላ