ቱርክሜኒስታን ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ ገልፃለች።
በቱርክሜኒስታን አስተናጋጅነት በተካሄደው 3ኛው የተመድ ባህር በር የሌላቸው በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ጉባኤን ተከትሎ በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ከቱርክሜኒስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራሺድ ሜሬዶቭ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱም አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) የባህር በር ጥያቄ በዝርዝር ያስረዱ ሲሆን ከ120 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ የጂኦግራፊ እስረኛ ሆና መቆየት እንደሌለባት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም ላይ በህዝብ ብዛት ትልቋ ወደብ የለሽ ሀገር እንደመሆኗ ውስብስብ በሆኑ የውስጥና የውጭ ሴራዎች ምክንያት ያጣችውን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የባህር በር ባለቤትነት በድጋሚ ለማግኘት እየሠራች መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ ይህንን የባህር በር ጥያቄ በሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ የዓለም አቀፍ ህግን መሰረት በማድረግ ለማስከበር ቁርጠኛ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ይህ ጥረት ለሀገራዊ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ለክልላዊ ውህደት፣ ልማትና ደህንነት ወሳኝ መሆኑን የገለፁት አምባሳደሩ፤ መንግስት እያንዳንዱን ፈተና ወደ መልካም አጋጣሚ ለመቀየር እንደሚሰራ አመልክተዋል።
የቱርክሜኒስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራሺድ ሜሬዶቭ በበኩላቸው፤ ሀገራቸው የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ እንደምትጋራ እና እንደምትደግፍ ገልፀዋል።
ቱርክሜኒስታን በክልላዊ ትብብር አስፈላጊነት እና እያንዳንዱ ሀገር የባህር በር የማግኘት መሰረታዊ መብት እንዳለው እንደምታምንም አረጋግጠዋል።
ሚኒስትሩ በተለይ ለኢቢሲ እንደገለፁት በሁለቱም ሀገራት የሚገጥሙ ተመሳሳይ ተግዳሮቶች እንዳሉ አንስተው፤ በሁሉም የባህር በር በሌላቸው ሀገራት መካከል ትብብር ከዛም ባለፈ ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አስምረውበታል።
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #Turkmenistan #seaaccess