Search

የቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የርህራሄ ዓሻራዎች

ማክሰኞ ሚያዝያ 06, 2018 101

በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ታሪክ ውስጥ "ቀዳማዊት እመቤት" የሚለው ስያሜ ከግርማዊነትና ከክብር ባለፈ፣ አዲስ ትርጉም እየያዘ መጥቷል። ይህ ስያሜ ዛሬ ላይ የዝምታ አገልግሎት፣ የትህትና ጉዞ እና የሰብዓዊነት መገለጫ ሆኖ በብዙዎች ልብ ውስጥ ሰርጿል።

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያሳዩት የማይነጥፍ ቁርጠኝነት አንድን ትልቅ እውነት በተግባር አረጋግጧል፤ "እናትነት በቤት ውስጥ አይወሰንም፤ የሀገር እናትነት ማለት የሌሎችን ህመም መጋራት፣ የጎደለውን መሙላት ነው" የሚለውን እውነት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) "መደመር" በሚለው ፍልስፍናቸው ኢትዮጵያውያን ተደጋግፈውና ተሳስረው እንዲያድጉ እንደሚወተውቱት ሁሉ፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውም ይህንን ራዕይ ወደ ማዕድ ማጋራት ተግባር ቀይረውታል። በመላው ኢትዮጵያ የተገነቡት 14 ግዙፍ የዳቦና የዱቄት ፋብሪካዎች የዚህ የ"መደመር" ፍሬ ህያው ምስክሮች ናቸው።

የቀዳማዊት እመቤት ፅሕፈት ቤት ከአጋር አካላት ጋር በትብብር የገነባቸው እነዚህ ፋብሪካዎች ተራ የኢንዱስትሪ ተቋማት አይደሉም። ይልቁንም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖች በዝቅተኛ ዋጋ የዕለት ጉርሳቸውን እንዲያገኙ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል ባለቤት እንዲሆኑ እና የገበያ ዋጋን በማረጋጋት የዜጎችን ሸክም እንዲያቃልሉ የታለሙ የተስፋ ማዕከላት ናቸው። ይህም "ማንም ኢትዮጵያዊ ሳይበላ ማደር የለበትም" የሚለውን የቀዳማዊት እመቤቷን ጽኑ መርህ ወደ ተግባር አውርዶታል።

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በዝምታና በትህትና የሚያከናውኑት ሥራ ውጤቱ ጮክ ብሎ እየተናገረ ነው። እንዲህ ዓይነት ሥራ ለመሥራት በእውነትም "የእናት ልብ" ሊኖር ይገባል። እሳቸው የገነቧቸው 14 የዳቦና የዱቄት ፋብሪካዎች፣ የአካል ጉዳተኞች መኖሪያ ቤቶች፣ የሕፃናት ማሳደጊያዎች እና 37 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሙሉ የሚመነጩት "መደመር" ከሚለው የፍቅር እና የአንድነት ምንጭ ነው።

የቀዳማዊት እመቤቷ አሻራ በዳቦ ፋብሪካዎች ብቻ አይወሰንም። እውቀት ለተጠሙ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት፣ የዓይን ብርሃናቸውን ላጡ ተስፋን በመለገስ እና ለተቸገሩት መጠለያ በመሆን ለሺዎች የብርሃን ጮራ ፈንጥቀዋል። በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ለሰው ልጅ እጅግ መሠረታዊ የሆነውን የዳቦ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ግንባር ቀደም በመሆን ታሪክ እየሠሩ ይገኛሉ።

የቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጉዞ "ሥልጣን ለወገን አገልግሎት" መሆኑን በተግባር ያስመሰከረ ነው። በዳቦ ፋብሪካዎች የሚታየው ተስፋ፣ የነገዋ ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ ማሳያ ነው። 

በላሉ ኢታላ

#EBC #Ethiopia #FirstLadyZinashTayachew #HumanitarianWork #Development #Medemer #BreadFactory