የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ ዳኛ አበበ ሰለሞን ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ከነሀሴ 1 ጀምሮ እስከ መስከረም 30 ፍርድ ቤቶች ዝግ መሆናቸው ለዳኞች እረፍት ለመስጠት ታስቦ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
አሰራሩ የመዝገብ ክምችትን ለመቀነስም ያለመ እንደሆነም ያነሳሉ፡፡
ዳኞች የዓመት እረፍት የሌላቸው በፈለጉት ጊዜ ቢወጡ ተገልጋይ እንዲጉላሉ ያደርጋል ተብሎ በመታሰቡም እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
በእነዚህ ሁለት ወራት የነበሩ መደበኛ የፍርድ ሂደቶች ይቀራሉ እንጂ፤ አንድ ሰው መብቱ ሲነካ፣ በደል ቢደርስበት ፍትህ ፈልጎ ፍርድ ቤት ቢመጣ ዝግ ይሆናል ማለት እንዳልሆነ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በወንጀል ጉዳዮች የዋስታና መብት፣ የጊዜ ጉዳይ ቀጠሮዎችን፣ የእስሩ ፍርዱን ያጠናቀቀ ታራሚ፣ ከእግድ ጋር የተያያዘ ጉዳይ እንዲሁም በቤተሰብ ጉዳይ የፍርድ ሂደት እንደማይቋረጥ ነው የጠቀሱት፡፡
የመዝገብ ክምችት እንዳይኖር ሂደቱን የሚያፋጥኑ አሰራሮች እንደሚሰሩም አመላክተዋል፡፡
ዳኛ አበበ ሰለሞን አክለውም፤ የዳኝነት አገልግሎት ጥራትን እና ቅልጥፍናን ለማረጋገጥ በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ለመፍጠር እንዲያስችል የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ላለፉት 2 አመታት ሲሰራ ቆይቶ በዚህ ዓመት መጠናቀቁንም አንስተዋል፡፡
ከፍርድ ቤት ወደ ተገልጋይ፤ ከተገልጋይ ወደ ፍርድ ቤት የሚኖሩ የመረጃ እና የሰነድ ልውውጦችን ወደ ዲጂታል ለመለወጥ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር በተመተባርም አሲሲ መተግበሪያ ማበልፀግ መቻሉንም ገልፀዋል፡፡
መተግበሪያው ስራ ሲጀመር ፍርድ ቤቶች ከክስ መክፈት እስከ ውሳኔ መስጠት እስከ ብያኔ ያሉ አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ ለማድረግ እንደሚያግዝም ኃላፊው አብራርተዋል፡፡
በሜሮን ንብረት
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #Court