ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አምራች ኢንዱስትሪ ለኢትዮጵያ ብልጽግና አይተኬ ሚና እንዳለው እና የኢኮኖሚው ልብ መሆኑን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በመደመር መንግሥት የሥራ አቅጣጫ ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ትልቅ ቦታ የሰጡበትን ዝርዝር ምክንያቶች አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አምራች ኢንዱስትሪን ከሰው ልጅ ልብ ጋር በማመሳሰል፣ “አንድ ሰው ልቡ ካልሠራ ሁሉ አካላቱ ጤነኛ ቢሆኑም ውጤታማ እንደማይሆን ሁሉ፣ ኢኮኖሚን ኢኮኖሚ የሚያደርገው የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ነው” ብለዋል።
ዘርፉ የዕድገት ሞተር ተብሎ የሚጠራውም በሌሎች ዘርፎች ውስጥ ከፍተኛ የምርታማነት ለውጥ ማምጣት ስለሚችል መሆኑን ጠቁመዋል።
ለአብነትም በግብርናው ዘርፍ የኢንዱስትሪ ውጤቶች የሆኑትን ትራክተር እና ማዳበሪያን መጠቀም ምርትን በጊዜ፣ በብዛት እና በጥራት እንደሚያሳድግ ገልጸው፣ ይህም ከባህላዊ አሠራር ወደ ዘመናዊ እና ከፍተኛ ገቢ ወደሚያስገኝ ሽግግር ለመሻገር ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
ለዘርፉ ቅድሚያ የተሰጠባቸውን አራት መሠረታዊ ምክንያቶች ሲዘረዝሩም፦
• ምርታማነት እና ኤክስፖርት፦ ኢንዱስትሪ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በከፍተኛ ደረጃ ከማሟላት ባለፈ፣ የውጭ ገበያ ስታንዳርድን የጠበቁ ምርቶችን በብዛት በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ቁልፍ ሚና ይጫወታል።
• መዋቅራዊ ሽግግር፦ ኢትዮጵያ ጥሬ ዕቃ ብቻ አቅራቢነት (ለምሳሌ ቡናን፣ ወርቅን እና ሊቲየምን ባለመቀነባበር መሸጥ) ወጥታ ወደ ተቀነባበሩ እና እሴት የተጨመረባቸው ምርቶች እንድትሸጋገር ያደርጋል።
• ፈጠራ እና ቴክኖሎጂ፦ ማኑፋክቸሪንግ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ዘርፎችም የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ምንጭ በመሆን እንደ ማስፈንጠሪያ “ስፕሪንግ ቦርድ” ያገለግላል።
• የሥራ ዕድል፦ ከሌሎች ዘርፎች በተለየ ሁኔታ ለዜጎች ሰፊ እና ተከታታይነት ያለው የሥራ ዕድል ይፈጥራል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ጉዳይ ከኢኮኖሚ ባለፈ ከሀገር ሉዓላዊነት ጋርም የተቆራኘ ነው።
የራሷን ምግብ፣ ልብስ እና መድኃኒት በበቂ ሁኔታ የማታመርት ሀገር ሉዓላዊነቷን ለማስከበር እና ፍላጎቶቿን ለመከላከል ትቸገራለች።
"ሉዓላዊ ለመሆን፣ የተሻገረ ኢኮኖሚ ለመፍጠር እና የምናስበውን ብልጽግና ለማምጣት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍን በበቂ ደረጃ መምራት እና ማሳካት ግዴታ ነው" ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል።
"የመደመር መንግሥት" እሳቤ በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ መካከል ያለውን ሚዛን በመጠበቅ፣ አንዱ ለሌላው መከታ ሆኖ የጋራ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሆነ እና ለዚህም ስኬት ኢንዱስትሪ ከመንግሥት አምስት ቁልፍ ዘርፎች አንዱ ሆኖ መቀመጡን ጠቁመዋል።
በዮናስ በድሉ
#EBC #Ethiopia #PMAbiyAhmed #industry #manufacturing