ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ዐሥር ዓመታት ውስጥ ያለ ጥርጥር የአፍሪካ አውራ ሀገር እንደምትሆን ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል።
ይህንን ታላቅ ራዕይ እውን ለማድረግ ግን በምኞት እና በልመና ሳይሆን፣ ችግርን ላለመውረስ ሌት ተቀን ያለመታከት መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ አሁን ላይ የሚሠራው ሥራ ለመጪው ትውልድ ጠንካራ መሠረት የሚጥል መሆኑን አብራርተዋል።
የአሁኑ ትውልድ የብልጽግናው ሙሉ ተቋዳሽ ባይሆንም፣ የትጋታቸው ምሥጢር ልጆቻቸው እና መጪው ትውልድ የበለጸገች ኢትዮጵያን እንደሚረከቡ ማመናቸው መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይ ሀገራችን ያለችበትን የለውጥ ፍጥነት እና እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶችን ብዙዎች በውል እንደማይረዱት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኢትዮጵያ ጉዞ እንደማይቆም እና መሠረታዊ ፍላጎቶችን ደረጃ በደረጃ እያሟላች ወደ ፊት እንደምትገሰግስ አረጋግጠዋል።
በሌላ በኩል "ሌብነት ሀገር አያሳድግም፣ አለመተጋት ሀገር አያሳድግም" በማለት፣ ሕዝቡ በንፁህ እጅ፣ በመደመር እና በጋራ ራዕይ ላይ አተኩሮ እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ከችግር፣ ከረሃብ እና ከእርዳታ ጠባቂነት ተላቅቃ፤ በዓለም መድረክ ከፍ ብላ የምትታይበት ጅማሮ በእጅ ላይ መሆኑንም አውስተዋል።
ይህንን ለማሳካት በንጹህ ልቦና እና በውጤት ሀገርን ለማቅናት በሚደረገው ጥረት ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
በለሚ ታደሰ