የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት ባለፉት 5 አመታት በመላው የሀገሪቱ ክፍሎች 35 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ገንብቶ በርካታ ተማሪዎች የትምህርት አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
ትምህርት ትውልድን ለማነጽና ለነገ አገር ተረካቢ የሆነን የተማረን ዜጋ ለማፍረት ወሳኝ ተግባር ነው ያለው ጽ/ቤቱ፤ በትምህርት ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ባለፉት 5 ዓመታት 35 ትምህርት ቤቶች መገንባቱን ገልጿል፡፡
የጥራት ደረጃቸው ተጠብቆ ከተገነቡ ዘመናዊ ት/ቤቶች ውስጥ አንዱ በአዲስ አበባ የሚገኘው ብርሃን የአይነሥውራን አዳሪ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት መሆኑን የጠቀሰው ጽ/ቤቱ፤ ትምህርት ቤቱ ከ400 በላይ የሆኑ ተማሪዎችን ከተለያዩ አካባቢዎች ተቀብሎ በማስተማር ላይ እንደሚገኝም ጠቁሟል፡፡
የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት የት/ቤቱን የመማር ማስተማር ሒደት፣ የት/ቤቱን እና የተማሪዎቹን ፍላጎት በቅርብ ክትትል በማድረግ በርካታ ተጨማሪ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑንም ነው የገለፀው፡፡
በዚህም በዛሬው ዕለት የመማር ማስተማር ሒደቱን ሊያቀላጥፉ የሚችሉ የብሬል ፕሪንተር (ኢምቦሰር) እና ዲጂታል ሪከርድስ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም በት/ቤቱ ውስጥ ለተማሪዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ ለሚገኘው ክሊኒክ የተለያዩ የሕክምና መሳሪያዎች እና መመርመሪያ ሪኤጀንቶችን ማበርከቱን ከጽ/ቤቱ የማህበራዊ ትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡