Search

ታላቁ ሰርጥ፡ ቀይ ባሕር

ዓርብ ሚያዝያ 09, 2018 93

ቀይ ባሕር ለሰው ልጅ ሥልጣኔና ለዓለም አቀፍ ንግድ መሠረት ከሆኑት ጥቂት የውኃ አካላት መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ስትራቴጂካዊ ሀብት ነው። ይህ በአፍሪካና በእስያ አህጉራት መካከል ተሸሽጎ የሚገኝ ጠባብ የባሕር ወለል ቢሆንም፣ የሚጫወተው ሚና ግን ከአካባቢያዊ ፋይዳ አልፎ አጠቃላይ የዓለምን ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ መረጋጋት የሚወስን የጂኦፖለቲካ የልብ ትርታ ሆኗል።  

የዚህ የውኃ መስመር ስትራቴጂካዊ ልዩነት የሚመነጨው በዓለም ላይ ካሉት እጅግ ወሳኝ የሆኑ የባሕር መተላለፊያዎችን ወይም ሰርጦችን (Chokepoints) በማገናኘቱ ነው። በደቡብ የባብ አል-መንደብንና በሰሜን የሱዊዝ ቦይን እንደ ሁለት መከፈቻ በሮች የሚጠቀም ሲሆን፤ እነዚህ መተላለፊያዎች ባይኖሩ ኖሮ የዓለም ንግድ ዛሬ ካለበት ፍጥነትና ቅልጥፍና እጅግ የራቀና ውድ በሆነ አማራጭ ውስጥ ይወድቅ ነበር።

ከሌሎች ታላላቅ የባሕር መተላለፊያዎች ጋር ሲነጻጸር ቀይ ባሕር ልዩ ባህሪ አለው። የሆርሙዝ ሰርጥ የዓለም የኃይል ምንጭ ተብሎ ቢታወቅም፣ ቀይ ባሕር ግን ከ4 እስከ 9 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ከማስተላለፉ ባለፈ፣ የዓለምን 12 በመቶ ንግድ የሚሸከም ሁለንተናዊ ድልድይ ነው። የማላካ ሰርጥ ከፍተኛ የመርከብ ትራፊክ ቢስተዋልበትም፣ ቀይ ባሕር አውሮፓን፣ እስያንና አፍሪካን በማስተሳሰር ረገድ የማይተካ ሚና አለው። የሱዊዝ ቦይ ደግሞ በአፍሪካ ዙሪያ የሚደረገውን የ8 ሺህ 900 ኪሎ ሜትር ረዥም ጉዞ በማስቀረት የጊዜና የገንዘብ ቁጠባ ዋነኛ ምንጭ ሆኗል።

የጥልቁ ባሕር ምስጢራት

ይህ የውኃ አካል ከመተላለፊያነቱ ባሻገር፣ በውስጡ የያዛቸውና ለብዙዎች ስውር የሆኑ ተፈጥሮአዊ ባህሪያት "ምስጢራዊ" እሴቶች እንዲኖሩት አድርገውታል። በጂኦሎጂካል አፈጣጠሩ የአፍሪካና የዓረብያ ጠፍጣፋ መሬቶች (Tectonic Plates) በየዓመቱ በአንድ ሴንቲ ሜትር ገደማ እየራቁ በመሄዳቸው የተፈጠረ በመሆኑ፣ ወደፊት ወደ አዲስ ውቅያኖስነት የመለወጥ ዕድል እንዳለው ሳይንሳዊ ግምቶች ያመለክታሉ።

ወደ ባሕሩ የሚገባ ምንም ዓይነት ወንዝ አለመኖሩና ከፍተኛ ሙቀት መኖሩ ውኃው እጅግ ጨዋማ (40 በመቶ) እንዲሆን አድርጎታል። "ቀይ ባሕር" የሚለውን ስያሜ ያገኘውም አልፎ አልፎ በውኃው ላይ ከሚታዩት "Trichodesmium erythraeum" ከተሰኙ ቀይ አልጌዎች ነው።

ከሁሉም በላይ የዓለምን ኃያላን ዓይን እንዲያርፍበት ያደረገው በወለሉ ውስጥ የሚገኙት ከፍተኛ የማዕድን ክምችቶች ናቸው። በተለይም "አትላንቲስ 2" (Atlantis II Deep) የተሰኘው ጥልቅ ስፍራ ከ3.11 እስከ 8.21 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚገመት ሀብት ይዟል። በዚህ ስፍራ ከ3.7 ሚሊዮን ቶን በላይ ዚንክ፣ 800 ሺህ ቶን መዳብ፣ 7 ሺህ ቶን ብርና 47 ቶን ወርቅ እንደሚገኝ ጥናቶች ያሳያሉ። በተጨማሪም ለማንጋኒዝ እና ለወደፊቱ የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ ምርት ወሳኝ የሆነው ኮባልት በከፍተኛ መጠን መገኘቱ፣ ባሕሩን የታላቅ የኢኮኖሚ ፉክክር ማዕከል ያደርገዋል።

የታሪክ ምስክሮችና የኢትዮጵያ የማይናወጥ ትስስር

ቀይ ባሕር ለዘመናት የታላላቅ ሥልጣኔዎች መገናኛ በመሆኑ በርካታ ምስጢሮችን ቀብሮ ይዟል። ጥንታዊቷ የአዱሊስ ወደብ የታላቁ የአክሱም ሥልጣኔ ዋነኛ የባሕር መተንፈሻ ነበረች። የአክሱም ነገሥታት ባሕሩን በመቆጣጠራቸው በዓለም ላይ ከነበሩት አራት ታላላቅ ኃያላን አንዱ ለመሆን በቅተዋል፤ ይህም የኢትዮጵያ ታላቅነት ከባሕር ዳርቻዋ ጋር ምን ያህል የተቆራኘ እንደነበረ ህያው ምስክር ነው።

ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋር ያላት ግንኙነት በካርታ ላይ በሚሰመር ድንበር ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን፣ በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት በደም፣ በአጥንትና በታሪክ የተሳሰረ የማንነት ውህድ ነው። ከአክሱም ዘመን ጀምሮ እስከ መካከለኛው ዘመን መሪዎች፣ እንዲሁም እስከ ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የቀድሞ ነገሥታትና መንግሥታት ድረስ፤ ሁሉም መሪዎች የሀገር ሉዓላዊነትና የኢኮኖሚ ነፃነት የሚረጋገጠው በባሕር በር ባለቤትነት መሆኑን በተግባር አሳይተዋል።

በአሁኑ ወቅት ቀይ ባሕር በወታደራዊ ካምፖች እጅግ የታጨቀ ቀጠና ሆኗል። ጎረቤት ሀገር ጅቡቲ የታላላቅ ሀገራትን ጦር ሰፈሮች በማስተናገድ የዓለም ጂኦፖለቲካዊ ላቦራቶሪ ሆናለች። ከ2024 እስከ 2025 ባሉት ዓመታት የተከሰቱት የጸጥታ ቀውሶች የባሕሩን ወሳኝነት ይበልጥ አጉልተውታል። የኮንቴይነር ትራፊክ በ75 በመቶ ሲቀንስ፣ የኢንሹራንስ ዋጋ በ1 ሺህ በመቶ ጨምሯል። ይህም የዓለምን ኢኮኖሚ ከማናጋቱም በላይ ከ8 ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ የባሕር ስፋትን ለብክለት ዳርጓል።

የወደፊት ዕጣ-ፈንታና የኢትዮጵያ የህልውና ጥያቄ

ወደ 2030 እና ከዚያ በኋላ ስንመለከት፣ የቀይ ባሕር ዕጣ-ፈንታ በሁለት መንገዶች ላይ ይገኛል፤ አንደኛው በቀጠናው ሀገራት መካከል የሚፈጠር ፍትሃዊ ትብብር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የኃያላን ግጭት ቀጠና ሆኖ መቀጠል ነው።

ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ያላት አንገብጋቢ ፍላጎት ከኢኮኖሚ ህልውና እና ከብሔራዊ ደኅንነት ጋር የተያያዘ ነው። ከ130 ሚሊዮን በላይ ለሚሆን ሕዝቧ የሚያስፈልጉ ምርቶችን ለማስገባትና ለማውጣት በሌሎች ሀገሮች ላይ ጥገኛ መሆኗ፣ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ወጪ በማስከተል በኢኮኖሚዋ ላይ ጫና ፈጥሯል። የራሷ የባሕር በር አለመኖሩ የሀገሪቱን የንግድ ሰንሰለት ለማንኛውም ፖለቲካዊ ለውጥ ተጋላጭ ስለሚያደርገው፣ የባሕር በር ማግኘት የብልፅግናዋ ብቻ ሳይሆን የደኅንነቷም ዋስትና ነው።

ታላቁ ሰርጥ ቀይ ባሕር ከታሪካዊው የአክሱም ሥልጣኔ ጀምሮ የጥንካሬና የብልፅግና መገኛ ሆኖ ቆይቷል። ኢትዮጵያ በዚህ ባሕር ላይ ያላትን ታሪካዊ መብት ለማስከበር የምታደርገው ጥረት የፍትሃዊነትና የህልውና ጥያቄ ነው። ይህንን የውኃ አካል የሰላምና የብልፅግና መድረክ እንዲሆን ማድረግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት ነው። ያለበለዚያ ግን ባሕሩ የኃያላን ግጭት መድረክና የአፍሪካ ቀንድ አለመረጋጋት ምንጭ ሆኖ የመቀጠል አደጋ ተጋርጦበታል።

 

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ