በኢትዮጵያ የፀጥታ ችግር ይስተዋልባቸው በነበሩ አካባቢዎች፤ በተሰራው ሰላምን የማፅናት ሥራ ውጤቶች እየታዩ መሆኑ ተገለፀ።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ኸይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ከኢቲቪ 57 ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የፀጥታ ችግር በነበረባቸው አካባቢዎች ሰላምን ለማስፈን፤ ቀጥተኛ ገፈት ቀማሽ ከሆነው ሕዝብ ጋር በየደረጃው ውይይት መደረጉን ጠቅሰዋል።
በውይይቶቹ ከምንይሽር ይልቅ በንግግር ችግሮች እንዲፈቱ የመፍትሔ ሀሳብ በማቅረብ ለሰላም በተደረገው ጥሪም በርካቶች ትጥቅ ፈተው ማህበረሰቡን ተቀላቅለዋል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው።
በዚህም ግጭት የነበረባቸው አካባቢዎች ከእለት ወደ እለት መሻሻል እየታየባቸው መሆኑን ገልፀው፤ እንደ ሀገርም አንፃራዊ ሰላም መስፈኑን ጠቁመዋል።
የሰላም ሚኒስቴር ይህን ሰላም ለማፅናት፤ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በጋራ እየሰራ እንደሆነም ገልፀዋል።
ለአብነትም በ4 ክልሎች የሃይማኖት ተቋማት ያደረጉት ውይይትን እና 70 ያህል የፖለቲካ ፓርቲዎች በቢሾፍቱ ሰላምን ለማፅናት የቢሾፍቱ ቃልኪዳንን ማርቀቃቸውን አንስተዋል።
ማህበረሰብ ተኮር ስብሰባዎች ከቀበሌ እስከ ክልል እና ሀገር አቀፍ ደረጃ እንደ ባህል እንዲያድግ መሠራቱንም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
ሰላም ለሁሉም የሀገር እንቅስቃሴ መሠረት በመሆኑ እንደ ሀገራዊ ምክክር ያሉ፤ ሰላም የሚያፀኑ ተቋማት ውጤት ኢትዮጵያ ሰላሟ ተጠብቆ ለትውልድ እንድትሻገር አስተዋጽኦው ትልቅ ነውም ብለዋል።
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #Peace