Search

ቀይ ባሕር፦ የኢትዮጵያ የብልጽግና በር

ረቡዕ ሚያዝያ 14, 2018 130

ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ የታሪክ ትውስታ ብቻ ሳይሆን፣ የአዲሲቱና የበለጸገችው ኢትዮጵያ የትንሣኤ መውጫና የህልውናዋ ዋስትና ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር በ2030 ወደ 150 ሚሊዮን እንደሚጠጋ በሚጠበቅበት ሁኔታ፣ ቀጥተኛና አስተማማኝ የባሕር በር አለመኖር የሀገራችንን የልማት ምኞት ቅርቃር ውስጥ የሚከት "ጂኦግራፊያዊ እስር ቤት" ተደርጎ ይወሰዳል ። በመሆኑም የቀይ ባሕር ጉዳይ ከትርክት ባለፈ፣ በኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ በማኅበራዊ ደኅንነትና በፖለቲካዊ ነፃነት ሚዛን ላይ የሚቀመጥ ወሳኝ የስትራቴጂ ጥያቄ ሆኗል ።  

የባሕር በር አልባነት የሚጠይቀው ውድ ዋጋ፡

ኢትዮጵያ ወደብ አልባ በመሆኗ ምክንያት በየዓመቱ የምትከፍለው ዋጋ እጅግ መራርና ሀገራዊ ዕድገቷን የሚያቀጭጭ ነው። ከጠቅላላ ሀገራዊ ምርቷ (GDP) ውስጥ ከ13 እስከ 23 በመቶ የሚሆነው ዕድገት የባሕር በር በማጣታችን ምክንያት ይባክናል። ይህ በገንዘብ ሲሰላ በዓመት ከ19 እስከ 31 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የዕድገት ዕድል ማጣት (Opportunity Cost) ነው። ይህ ግዙፍ ሀብት የባሕር በር ቢኖረን ኖሮ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎች ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤትና ፋብሪካ በሆነ ነበር።

የወደብና የሎጂስቲክስ ክፍያዎች ብቻቸውን በዓመት እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚወስዱ ሲሆን፣ ዕለታዊ የትራንዚት ወጪያችንም 5 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል። ይህ ሁኔታ በገበያ ላይ በሚታዩ ሸቀጦች ዋጋ ላይ ቀጥተኛና አውዳሚ ተፅዕኖ አለው። የባሕር በር ርቀትና የወደብ ኪራይ በገቢና ወጪ ንግድ ምርቶቻችን ላይ ከ20 እስከ 30 በመቶ የሚደርስ ተጨማሪ "የወደብ ታክስ" ይጭናል። ይህ ማለት አንድ ኢትዮጵያዊ ለልጆቹ የሚገዛው የምግብ ዘይት፣ አልባሳትና የቤት ቁሳቁሶች ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ እንዲኖር በማድረግ ማኅበራዊ ጫናውን መሪር ያደርገዋል።

ይባስ ብሎም፣ በወደብ መውጫና በሎጂስቲክስ መጓተት ምክንያት የሚከሰተው የመድኃኒቶች መበላሸት የዜጎቻችንን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ነው። ለዜጎች ጤና ወሳኝ የሆኑ እንደ ኢንሱሊንና ክትባቶች ያሉ መድኃኒቶች በወደብ ላይ በሚፈጠር መቆራረጥና ሙቀት ምክንያት ጥራታቸውን በማጣት ለብክነት ይዳረጋሉ። ይህ ኪሳራ በዶላር ብቻ የሚሰላ ሳይሆን፣ በወገኖቻችን ሕይወትና ጤና የሚከፈል መሪር መስዋዕትነት ነው። በአንድ ወደብ ላይ ብቻ ያለው 95 በመቶ ጥገኝነት፣ የሎጂስቲክስ ሰንሰለቱ ላይ ፉክክር እንዳይኖር በማድረግ ወጪን ከማናሩ ባለፈ፣ ለስትራቴጂካዊ ተጋላጭነት ዳርጎናል። አማራጭ የባሕር በሮች ቢኖሩን ኖሮ፣ ይህ ወጪ እስከ 40 በመቶ በመቀነስ የኑሮ ውድነቱን ማቅለል ይቻል ነበር።

የምግብ ሉዓላዊነትና የዲጂታል ደኅንነት

የቀይ ባሕር ጥያቄ ከምግብ ሉዓላዊነታችን ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ነው። ለግብርና ምርታማነት ወሳኝ የሆኑት ማዳበሪያና የቴክኖሎጂ ግብዓቶች በወደብ መጓተትና በከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ ምክንያት ገበሬው ዘንድ ዘግይተውና በውድ ዋጋ ይደርሳሉ። ይህ ደግሞ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እንቅፋት ይሆንበታል። የባሕር በር ቢኖረን ኖሮ፣ ሰማያዊ ኢኮኖሚውን (Blue Economy) በመጠቀም የቀይ ባሕርን የዓሣ ሀብት ለምግብ ዋስትናችን ማዋል ይቻል ነበር።

በዘመናዊው ዓለም ደግሞ የቀይ ባሕር አስፈላጊነት ወደ ዲጂታል ሉዓላዊነትም ይሻገራል። ዓለምን የሚያገናኙ ግዙፍ የኢንተርኔትና የመረጃ ባሕር ውስጥ ሰርጓጅ ኬብሎች የሚያልፉት በዚህ ቀጣና ነው። ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ያላት ድርሻና ተጽዕኖ መላላት፣ የዲጂታል ደኅንነቷና የመረጃ ፍሰቷ በሌሎች ኃይሎች ቁጥጥር ስር እንዲወድቅ ያደርገዋል። የዲጂታል ኢኮኖሚዋን ለመጠበቅና አስተማማኝ የመረጃ ትስስር እንዲኖራት፣ የቀይ ባሕር መዳረሻ ወሳኝ ነው።

የሉዓላዊነትና የስትራቴጂካዊ ነፃነት ጥያቄ

ቀይ ባሕርን የመጠቀም መብት ከኢኮኖሚ ባለፈ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ነፃነትና የቀጠናዊ ተሰሚነት ቁልፍ መሣሪያ ነው። 130 ሚሊዮን ሕዝብ ይዛ በአንድ መውጫ በር ላይ ብቻ መቆለፍ፣ የሀገራችንን የውሳኔ ሰጪነት አቅም ይገድባል። የቀይ ባሕር መውጫ መኖር ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድና በዓለም አቀፍ የባሕር መስመሮች ላይ ያላትን ተሰሚነት ከፍ በማድረግ፣ እንደ ትልቅ ሀገር የሚገባትን የጂኦ-ፖለቲካዊ ክብደት እንድታገኝ ያደርጋታል።

ከዚህም ባለፈ፣ በቀጣናው የሚታየውን የባሕር ላይ ውንብድና እና የሽብር ስጋት ለመመከት፣ የንግድ መርከቦቻችንን ደኅንነት ለመጠበቅና ለቀጠናዊ ሰላም ግንባታ አስተዋፅኦ ለማድረግ የባሕር ኃይል መገንባት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ይህ የባሕር ኃይል የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ ባለፈ፣ ለቀይ ባሕር ጸጥታ ዋስትና የሚሆን ታላቅ ኃይል ነው።

ኢትዮጵያ የባሕር በር መብቷን የምትጠይቀው በዓለም አቀፍ ሕጎች (UNCLOS Article 125) መሠረት ወደብ አልባ ሀገራት ወደ ባሕር የመድረስና የመጠቀም መብት እንዳላቸው በማመን ነው።  ይህ ስትራቴጂ የቀይ ባሕር ቀጠናን ከግጭት ቀጠናነት ወደ የጋራ ብልጽግና ማዕከልነት ለመለወጥ ያለመ የሰላም ጥሪ ነው።

በአጠቃላይ ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ የምኞት ጉዳይ ሳይሆን የህልውና መሠረት ነው። የባሕር በር አለመኖር በነፍስ ወከፍ በዓመት እስከ 35 ሺህ ብር የሚደርስ የደኅንነት ኪሳራ በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ እያደረሰ ይገኛል። ይህ መቆም አለበት። የሀገራችን የብልጽግና በር ለመክፈት፣ ሸቀጦችን በዝቅተኛ ዋጋ ለዜጎች ለማቅረብ፣ የመድኃኒት ብክነትን በማስቀረት የዜጎችን ጤና ለመጠበቅና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ስልታዊና አስተማማኝ የባሕር በር ማግኘት የግዜው አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። ይህ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድና በዲፕሎማሲ የሚመለስ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን መላው የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና የዓለም የኢኮኖሚና የሰላም ማዕከል የመሆን ዕድል ይኖረዋል። ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር በኩል ዓለምን የምታይበትና በብልጽግና የምትደምቅበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ