Search

"ተገልጋይን አክብሮ፣ ስቆና እጅ መንሻን አስቀርቶ አገልግሎት መስጠት ቀላል የማይባል የባህል ለውጥ ይጠይቃል"፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ረቡዕ ሚያዝያ 14, 2018 77

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረጅም ዘመናት ከቆዩብን ዋና ዋና ማነቆዎች አንዱ በመንግሥትም ሆነ በግል ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶች የተገልጋይን እርካታ ማረጋገጥ አለመቻላቸው ነው።

ለበርካታ አስርት ዓመታት የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ለማድረግ ጥረት ቢደረግም፣ ውጤታማ ሊሆን ያልቻለበት ዋናው ምክንያት ለረጅም ጊዜ የቆየውን ተቋማዊና ግለሰባዊ ባህል ቀይሮ፣ እጅ መንሻን አስቀርቶና ተገልጋይን አክብሮ አገልግሎት መስጠት የሚጠይቀውን ስር ነቀል የባህል ለውጥ ማምጣት ባለመቻሉ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ገልጸዋል።

ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥት ቴክኖሎጂን ከዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ አድርጎ በመቅረፅ፣ አገልግሎትን ዲጂታላይዝ የማድረግና ለተገልጋዩ ይበልጥ ተደራሽ የማድረግ ሥራዎችን በስፋት እያከናወነ ይገኛል።

በአንድ ማዕከል በርካታ አገልግሎቶችን የመስጠት ሥራ ከተጀመረ ገና አንድ ዓመት ገደማ ቢሆነውም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ 45 ማዕከላትን መክፈት ተችሏል።

እስከ መስከረም ወር ድረስም እነዚህ ማዕከላት ከመቶ በላይ እንደሚደርሱና እንደ ልደት ምስክር ወረቀት፣ የንግድ ፈቃድና ፓስፖርት ያሉ 3 ሺህ በላይ የሚሆኑ ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ እንዲሰጡ ይደረጋል።

ከዚህ በተጨማሪም አገልግሎትን ይበልጥ ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ በዘመናዊ የኤሌክትሪክ መኪናዎች የሚሰጠው "መሶብ" የሞባይል አገልግሎት ትልቅ ለውጥ እያመጣ ይገኛል።

እነዚህ ተንቀሳቃሽ ማዕከላት ዩኒቨርሲቲዎች፣ ገበያ ስፍራዎች እና ሰዎች በብዛት በሚገኙባቸው አካባቢዎች ድረስ በመሄድ ዜጎች ባሉበት ቦታ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋል።

አገልግሎቶችን ይበልጥ ለማቀላጠፍና ደህንነታቸውን ለመጠበቅ የዲጂታል መታወቂያ ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም የፋይናንስ አገልግሎትን፣ የጤና ፍላጎቶችን እና ንግድን ለማሳለጥ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል።

በአፍሪካ ፈር ቀዳጅ የሆነው ይህ የመንግሥት የቴክኖሎጂ ጣልቃ ገብነት ዜጎች ከቤታቸው ሳይወጡ ወይም ባሉበት ቦታ ሆነው አገልግሎት የሚያገኙበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።

አገልግሎት ከታነቀ ብልፅግናን ማረጋገጥ እንደማይቻል የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዜጎች ከእያንዳንዱ አገልግሎት የሚያተርፉት ጥቂት ደቂቃዎች ለሀገር ምርታማነትና ለግል ስኬት ትልቅ ትርጉም እንዳላቸው አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ካለችበት አታካች የአገልግሎት አሰጣጥ ባህል ወጥታ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘና የተገልጋይን ክብር የጠበቀ ሥርዓት ለመዘርጋት የጀመረችው ጉዞ ተስፋ ሰጪና አመርቂ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

በጌቱ ላቀው