Search

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከታሪክ ቁጭት ወደ ሀገራዊ የህልውና ግዴታ

ረቡዕ ሚያዝያ 14, 2018 78

ለዘመናት በቀይ ባሕር ላይ ግርማ ሞገስ የነበራትና የባሕር ኃይሏም የቀጣናው ዘብ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ ዛሬ የባሕር በር አልባ መሆኗ ብሔራዊ ቁጭት ሆኖ ቆይቷል። 

ይህ ሁኔታ በአጋጣሚ የተከሰተ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ስልታዊ የበላይነት ለመስበር የተደረገ የረዥም ዘመን የጂኦፖለቲካዊ ሴራ ውጤት መሆኑን የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ። 

በአሁኑ ወቅት ይህ ቁጭት ወደ አዲስ ብሔራዊ ወኔ በመቀየር፣ ሀገራችን በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ባለቤት ለመሆን የምታደርገው ጥረት የህልውናዋ መሠረት እየሆነ መጥቷል። 

አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ሌንጮ ለታ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታጣ የተደረገበትን ሂደት ሲያብራሩ፤ የኤርትራ ነፃ አገር መሆንን ተከትሎ ድንበር ሲካለል ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዳይኖራት ታስቦበት የተሰራ ሴራ መሆኑን ያስታውሳሉ። 

በወቅቱ ኢትዮጵያን ይመራ በነበረው መንግሥት ውሳኔ መሠረት መፈጸሙ፣ ሀገራችን በገዛ ደጇ ላይ እንደ ባዕድ ተመልካች አድርጓታል። ይህም በሚሊዮኖች ልብ ውስጥ ጥልቅ ቁጭት ፈጥሮ ማለፉን አቶ ሌንጮ ይገልጻሉ።

የባሕር በር አልባ መሆን ከታሪክ ቁጭት ባለፈ፣ በየዓመቱ ለቢሊዮኖች ዶላር የውጭ ምንዛሬ ወጪ በመዳረግ በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና ፈጥሯል። 

አቶ ሌንጮ እንደሚያነሱት፤ ኤርትራ ነፃ ስትወጣ የኢትዮጵያ ሕዝብ 50 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን ወደ 130 ሚሊዮን ተጠግቷል። 

የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ባለበት በዚህ ወቅት፣ የባሕር በር አለመኖር የሚያስከትለው የኢኮኖሚ መታፈን ይበልጥ አሳሳቢ ሆኗል። 

በመሆኑም ኢትዮጵያ ከዚህ ማነቆ ለመውጣት የራሷ የባሕር በር የግድ እንደሚያስፈልጋት አጽንኦት ሰጥተዋል።

የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት በአሁኑ ጊዜ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ አዲስ ብሔራዊ ንቅናቄ እየፈጠረ ይገኛል። ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት፣ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገርን ለማስረከብ ካለ ጥልቅ ፍላጎት የመነጨ ነው። 

አቶ ሌንጮ አክለውም፣ ይህ የባሕር በር የማግኘት እንቅስቃሴ በውይይት እና በ"ጥቶ መቀበል" መርህ ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበት ጠቁመው፤ የአሁኑ ትውልድ ዓላማውን የመደገፍ የዜግነት ግዴታ እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ የቅንጦት ሳይሆን የታሪክ ፍትሕ እና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ጉዳይ ነው። ዛሬ በሰላማዊ መንገድ እየተደረገ ያለው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት፣ ትናንት የተነጠቁ ዕድሎችን ዳግም ለመመለስ እና ኢትዮጵያ በቀጣናው የኢኮኖሚ ማማ የመሆን ሕልሟን ለማሳካት የሚደረግ የታሪክ ጉዞ ነው። 

ይህ የትውልድ ጉዞ በስኬት ከተጠናቀቀ፣ ሀገራችን ያላትን ሰፊ የሰው ኃይልና የተፈጥሮ ጸጋ ተጠቅማ በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን የጂኦፖለቲካዊ ሚና ዳግም ከፍ እንደምታደርግ ጥርጥር የለውም። 

በሃይማኖት ከበደ