Search

ኢትዮጵያ የተረከበችው የአፍሪካን የቴክኖሎጂ ሽግግር የመምራት ታሪካዊ ኃላፊነት

ሓሙስ ሚያዝያ 15, 2018 61

ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያ ያስመዘገበቻቸው ዘርፈ ብዙ ውጤቶች እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት በዓለም አቀፍ መድረኮች በተከታታይ ዕውቅና እየተሰጣቸው ይገኛል።
እነዚህ ዕውቅናዎች ሀገራችን ከእርዳታ ጠባቂነት ወደ መፍትሔ አፍላቂነት፣ ከኋላ ቀር ግብርና ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም ከአካባቢ መራቆት ወደ አረንጓዴ ልማት እያደረገች ያለችው መዋቅራዊ ሽግግር ማሳያዎች ናቸው።
አፍሪካ በአዲሱ የቴክኖሎጂ ምኅዳር ውስጥ የራሷን አሻራ ለማሳረፍ በምትተጋበት በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን የአህጉሪቱ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና የዲጂታል ጤና መሪ አድርጎ መሰየሙን ይፋ አድርጓል።
የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት እና የሰው ሠራሽ አስተውሎት መሪነት
ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የያዘችው ራዕይ በዛሬው ዕለት በአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ በተሰጠው የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) የዲጂታል ጤና መሪነት ዕውቅና ተረጋግጧል።
ይህ ሹመት ሀገራችን በዘርፉ እየሠራቻቸው ያሉ ተጨባጭ ለውጦችን ከግምት ያስገባ ነው። ኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም የአፍሪካ የመጀመሪያውን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት በማቋቋም በዘርፉ ከፍተኛ እምርታ እያሳየች ትገኛለች።
ሽልማቱ ኢትዮጵያ በዓለም ሁለተኛውን፣ በአፍሪካ ደግሞ የመጀመሪያውን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ለመክፈት ያላትን ዝግጅትም ታሳቢ ያደረገ ነው። ይህም አህጉሪቱ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የራሷን ዕጣ ፈንታ እንድትወስን እና ቴክኖሎጂን ለሰላም፣ ለጤና እና ለልማት እንድታውል ከፍተኛ የፖለቲካ ቁርጠኝነት የሚፈጥር ነው።
የግብርና ሽግግር እና የስንዴ ልማት ስኬት
ኢትዮጵያ ከስንዴ አምጪነት ወደ ላኪነት የተሸጋገረችበት ስኬት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አድናቆትን ያስገኘ ሌላኛው የሽግግር ማሳያ ነው።
በጥር 2024 (እ.አ.አ) የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት (FAO) የድርጅቱን ከፍተኛ የክብር ሜዳሊያ የሆነውን "አግሪኮላ ሜዳሊያ" (Agricola Medal) ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አበርክቷል።
ሽልማቱ የተሰጠው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምግብ ዋስትና፣ ለሥርዓተ ምግብ መሻሻል እና በተለይም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ላሳዩት ልዩ ቁርጠኝነትና ፈጣን አፈጻጸም ነው።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛውን ስንዴ ወደ ውጭ በመላክ ቀዳሚ ሀገር መሆኗ የመሪነቱን ውጤታማነት ያረጋግጣል።
የአረንጓዴ ዐሻራ እና የአካባቢ ጥበቃ ተምሳሌትነት
በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የአካባቢ ጥበቃ ተምሳሌት እንድትሆን አስችሏታል።
እስካሁን ድረስ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ ይህም የኢትዮጵያን የደን ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮታል።
በዚህ ውጤት ምክንያት በጥቅምት 2025 (እ.አ.አ) የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (FAO) ለኢትዮጵያ በ"ዘላቂ የደን አስተዳደር እና አጠቃቀም" ዘርፍ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ሰጥቷል።
ከዚህም በተጨማሪ በታኅሣሥ 2022 (እ.አ.አ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዋሽንግተን ዲሲ "የላቀ የአፍሪካ መሪነት ሽልማት" (Outstanding African Leadership Award) ተሰጥቷቸዋል።
የቱሪዝም እና የከተማ ዘመናዊነት ሽግግር
በቱሪዝም ዘርፍ የተከናወኑት ገበታ "ገበታ ለሸገር"፣ "ገበታ ለሀገር" እና "ገበታ ለትውልድ" ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ እያደረጓት ይገኛሉ።
ይህንንም ተከትሎ መስከረም 2024 (እ.አ.አ) የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (IGAD) ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለሦስት ዓመታት የሚቆይ የ"IGAD ቱሪዝም ሻምፒዮን" አድርጎ መርጧቸዋል።
የመደመር ፍልስፍና እና ብሔራዊ አሻራ
እነዚህ ተከታታይ ዓለም አቀፍ ዕውቅናዎች ኢትዮጵያ የተከተለችው የ"መደመር" ፍልስፍና በተግባር ውጤት እያመጣ መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው።
ሀገራችን በፈታኝ ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ውስጥም ቢሆን የራሷን የልማት አቅጣጫ ቀርፃ ስኬታማ መሆን እንደምትችል ለዓለም አሳይታለች።
ከምግብ ዋስትና እስከ ቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት የተገኘው ዕውቅና፣ ኢትዮጵያ በአህጉራዊ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላትን ተሰሚነት ከፍ ከማድረጉም በላይ፣ ለቀጣዩ ትውልድ ተስፋን የሚዘራ ታላቅ ብሔራዊ ዐሻራ ነው።
በለሚ ታደሰ