Search

የኢትዮጵያ ዲጂታል ሽግግር እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አፍሪካዊ ራዕይ

ሓሙስ ሚያዝያ 15, 2018 256

ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በቴክኖሎጂው ዘርፍ የጀመረቻቸው ሰፋፊ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ለሀገር በቀል ዕድገት ብቻ ሳይሆን ለአህጉራዊ መነቃቃት ፋና ወጊ ሆነው ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና የዲጂታል ጤና መሪ ሆነው መሾማቸው፣ ሀገራችን በዘርፉ የደረሰችበትን ደረጃ የሚያሳይ ትልቅ አህጉራዊ ዕውቅና ነው።

ይህ ሽግግር ኢትዮጵያን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ የፈጠራ ማዕከል እያደረጋት የሚገኝ ሲሆን፣ የዲጂታል ሽግግርን ለሥራ ቅልጥፍና፣ ለአካታች ዕድገት እና ለሉዓላዊነት ቁልፍ መሣሪያ አድርጋ መጠቀሟንም ያረጋግጣል።

1. ተግባራዊ ሉዓላዊነት እና የራስ ትርክት ባለቤትነት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአፍሪካ መድረኮች በሚያደርጓቸው ንግግሮች አፍሪካ ከቆየው የፖለቲካዊ አንድነት መንፈስ ወደ ተግባራዊ ሉዓላዊነት (Functional Sovereignty) መሸጋገር እንዳለባት በተደጋጋሚ አሳስበዋል።

ሉዓላዊነትን የራሳችንን ትርክት ከመፍጠር ጋር በማያያዝም፣ የራሳችንን ታሪክ ካልነገርን ልማታችን የተሟላ እንደማይሆን በፅኑ ይገልጻሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፣ “ሉዓላዊነት ማለት የራሳችንን ትርክት (Narrative) መፍጠር ማለት ነው፤ የራሳችንን ታሪክ ካልነገርን ልማታችን የተሟላ አይሆንም” ይላሉ።

ይህ አስተሳሰብ ኢትዮጵያ የራሷን ዳታ እና የቴክኖሎጂ ውጤቶች በራሷ ለመቆጣጠር የምታደርገውን የዲጂታል ሉዓላዊነት ትግል የሚወክል ሲሆን፣ የውጭ ቴክኖሎጂ ጥገኝነትን በመቀነስ ሀገር በቀል የሰው ሠራሽ አስተውሎት ውጤቶችን ማልማት የሀገርን ክብርና ታሪክ በራስ ቋንቋና መንገድ ለመንገር እንደሚያስችልም ይታመናል።

2. ተቋማዊ መሠረት፦ ከኢንስቲትዩት እስከ ዩኒቨርሲቲ

ኢትዮጵያ ለሰው ሠራሽ አስተውሎት የሰጠችው ትኩረት በተጨባጭ ተቋማዊ መሠረት ላይ ያረፈ ለመሆኑ በ2012 ዓ.ም የተቋቋመው የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋነኛው ማሳያ ነው።

ይህ ተቋም በአጭር ጊዜ ውስጥ በአፍሪካ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ ተቋማት አንዱ ለመሆን የቻለ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ በዓለም ሁለተኛው በአፍሪካ ደግሞ የመጀመሪያው የሆነውን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ለመክፈት ዝግጅት ተጠናቅቋል።

ዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ እስከ አንድ ሺህ ከፍተኛ ባለሙያዎችን ለማፍራት ከማቀዱም በላይ፣ 100 ለሚሆኑ አፍሪካውያን ተማሪዎች ነፃ የትምህርት ዕድል በመስጠት ኢትዮጵያን የአህጉሪቱ የቴክኖሎጂ ዕምብርት የማድረግ ታላቅ አህጉራዊ ራዕይ ሰንቋል።

3. የዲጂታል ጤና መሪነት ዕውቅና ምንጭ

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የዲጂታል ጤና መሪ እንድትሆን ካበቋት ስኬቶች መካከል በጤናው ዘርፍ ተግባራዊ የተደረጉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተጠቃሾች ናቸው።

በተለይም በራቀ ቦታ ለሚገኙ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች የሕክምና መመሪያዎችን በሀገር ውስጥ ቋንቋዎች የሚሰጠው "HEP Assist" የተሰኘው ቴክኖሎጂ አላስፈላጊ ሪፈራሎችን በመቀነስ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

በተጨማሪም በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች የበለጸገው እና 95 በመቶ ትክክለኛነት ያለው የጡት ካንሰር ምርመራ (AI Diagnostics) ቴክኖሎጂ፣ በሽታውን አስቀድሞ በመለየት ረገድ በዘርፉ የታየ ትልቅ የፈጠራ ውጤት ተደርጎ ይወሰዳል።

4. ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) በሌሎች ዘርፎች፦ ከግብርና እስከ ፍትሕ ሥርዓት

ከዲጂታል ጤና ባለፈ፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎት በሌሎች የኢትዮጵያ ቁልፍ የልማት ዘርፎች ላይም ትልቅ ለውጥ እያመጣ ይገኛል።

በግብርናው ዘርፍ የሰብል በሽታዎችን በምሥል በመለየት ቅድመ ማስጠንቀቂያ የሚሰጡ እና የአፈር ምርታማነትን የሚተነትኑ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) መተግበሪያዎች አርሶ አደሩን እያገዙ ሲሆን፣ ይህም የሀገራችንን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ያፋጥነዋል።

በቋንቋው ዘርፍ ደግሞ እንደ "ET Learning" ያሉ ሀገር በቀል የቋንቋ ሞዴሎች የዲጂታል አካታችነትን ከማረጋገጣቸውም በላይ የትርክት ሉዓላዊነትን እያጠናከሩ ነው።

ከዚህም ባለፈ በፍትሕ ሥርዓቱ የሰነድ ምርመራን ለማቀላጠፍ እንዲሁም በፋይናንስ ዘርፍ በ"ቴሌብር" እና ሌሎች ዲጂታል ግብይቶች አማካኝነት የደንበኞችን የዱቤ አገልግሎት ለመተንተን እና ደኅንነትን ለመጠበቅ ቴክኖሎጂው በስፋት ሥራ ላይ እየዋለ ይገኛል።

5. የሰው ኃይል ግንባታ እና መሠረተ-ልማት

የኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግር በ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂ እየተመራ ሲሆን፣ በሰው ኃይል ግንባታና በመሠረተ-ልማት ዝርጋታ ላይ ትልቅ ትኩረት ሰጥቷል።

የ5 ሚሊዮን ኮደሮች መርሐ-ግብር ወጣቶችን በዲጂታል ክህሎቶች በማሰልጠን ኢትዮጵያን የዕውቀት አገልግሎት ላኪ (skill exporter) ሀገር ለማድረግ እየሠራ ሲሆን፣ እስከ አሁንም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች የሥልጠናው ተጠቃሚ ሆነዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ከ41 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የተመዘገቡበት የ"ፋይዳ" ዲጂታል መታወቂያ እና 58 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ያሉት የ"ቴሌብር" የክፍያ ሥርዓት የሀገራችን የዲጂታል ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በመሆን እያገለገሉ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፍሪካ ሕብረት ንግግራቸው እንዳሉት፣ "እስከ 2063 አፍሪካ በምናስከብረው፣ በምናስቀጥለው እና ለሌሎች በምናካፍለው ነገር ትታወቃለች"።

ኢትዮጵያ ዛሬ የጀመረችው የቴክኖሎጂ ጉዞ፣ ሀገራችን ቀደምት አባቶቿ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዳደረጉት ሁሉ፣ በዲጂታል ዘመንም የአፍሪካ የኩራት ምልክት እና የለውጥ ሞተር እንድትሆን እያደረጋት ይገኛል።

ይህ ስትራቴጂያዊ ጉዞ ኢትዮጵያን በአፍሪካ የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት ግንባር ቀደም ተምሳሌት አድርጓታል።

በለሚ ታደሰ

#Ethiopia #digitalethiopia #AU #AbiyAhmed #AI #digitalhealth #EBC