Search

የቀይ ባሕር ሞገድ፦ በስትራቴጂካዊ ትንሣኤ ዋዜማ

ዓርብ ሚያዝያ 16, 2018 503

ቀይ ባሕር ለዘመናት የሰው ልጅ የንግድ ልውውጥና የሥልጣኔ መገናኛ ድልድይ ሆኖ ቢቆይም፣ በዛሬው ዘመን ግን ከወደብ አገልግሎት ባለፈ የዓለም አቀፍ ኃይሎች የጡንቻ ማሳያና የጥቅም ሽኩቻ ማዕከል ሆኗል። ይህ ጠባብ የባሕር መስመር ለኢትዮጵያ የብሔራዊ ደኅንነት ዋስትና፣ የኢኮኖሚ መተንፈሻና የቀጣናዊ መሪነት ማረጋገጫ በመሆኑ፣ በአካባቢው የሚታየው እጅግ የተወሳሰበ የጸጥታ ስጋትና የኃይሎች አሰላለፍ ለኢትዮጵያ የህልውና ያህል የሚታይ ጉዳይ ነው።

በአሁኑ ወቅት ቀይ ባሕር የዓለማችን ከፍተኛ ወታደራዊ ካምፖች ክምችት የሚገኝበት ስፍራ ሆኗል፤ ይህ የውጭ ኃይሎች መሠባሰብ የሀገራችንን የውሳኔ ሰጪነት ነፃነት ሊገድብ የሚችልና ቀጣናውን ለባዕዳን ፍላጎት ተገዢ የሚያደርግ "ስትራቴጂካዊ ከበባ" የመፍጠር ስጋት አለው።

በቀጣናው የሚስተዋለው የሽብር ቡድኖች መሠባሰብና ትስስር ደግሞ የጸጥታውን ስጋት ይበልጥ አሳሳቢና መጋፈጥ የሚገባው እውነት ያደርገዋል። በየመን የሚንቀሳቀሱት የሁቲ አማፂያንና በሶማሊያ የሚገኘው አል-ሸባብ የፈጠሩት "ተግባራዊ ትስስር" በቀይ ባሕርና በኤደን ባሕረ ሰላጤ አካባቢ አዲስ የጸጥታ ቀውስ ደቅኗል። እነዚህ ቡድኖች የመሣሪያ ዝውውርን፣ የድሮን ቴክኖሎጂ ሽግግርንና የባሕር ላይ ጥቃቶችን በማስተናበር፣ ዓለም አቀፍ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት በመሰንዘር የባሕር መስመሩን ለከፍተኛ አደጋ አጋልጠዋል።

ይህ ሁኔታ ለኢትዮጵያ በአንድ በኩል፣ 95 በመቶ የውጭ ንግዷን በቀይ ባሕር መስመር ላይ ያደረገችው ኢትዮጵያ፣ የመርከቦች መድን ዋጋ መጨመርና የሎጂስቲክስ መስተጓጎል የኑሮ ውድነትንና የኢኮኖሚ መቀዛቀዝን እያስከተለባት ይገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ በአል-ሸባብ የሚመራው የሽብር ስጋት በቀጥታ የኢትዮጵያን ድንበር የሚፈታተን ነው። 

የቀጣናው ኃይሎች አሰላለፍም ቢሆን ወጥነት የሌለውና በየጊዜው የሚለዋወጥ በመሆኑ፣ "የባሕር ጠረፍ ሀገራት ጥምረት" በቀይ ባሕር ላይ ያላቸውን የበላይነት ለማረጋገጥና እንደ ኢትዮጵያ ያሉ "ባሕር አገናኝ" ሀገራትን ተፅዕኖ ለመግታት ጥረት ሲያደርግ ተስተውሏል። ይህ አሰላለፍ በተለይም ከዓባይ ውኃ ክፍፍልና ከቀጣናዊ የበላይነት ሽኩቻ ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲያዊ የማግለል ሙከራ ቢያደርግም፣ ኢትዮጵያ ከቡድኑ በላይ ገዝፋ በመገኘቷ ተፅዕኖውን መሻገር ችላለች።

ኢትዮጵያ ያላት ግዙፍ የሕዝብ ቁጥር፣ እያደገ የመጣው ኢኮኖሚና የሰላም ማስከበር ሚናዋ ሀገራችንን በቀጣናው ፖለቲካ ውስጥ "የማይገፋ ኃይል" (Indispensable power) እንድትሆን አድርጓታል። በመሆኑም ይህ መሠባሰብ ኢትዮጵያን ከመገደብ ይልቅ፣ በብልህ ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያን አስፈላጊነት ይበልጥ ጎልቶ እንዲወጣ አድርጓል።

በዚህ በተግባራዊ ፖለቲካ በሚመራ ዓለም ውስጥ፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት ከታሪክ ናፍቆት ይልቅ በኢኮኖሚና በጸጥታ አስፈላጊነት ላይ የተመሠረተ ነው። ኢትዮጵያ በየዓመቱ ወደብ አልባ በመሆኗ ብቻ 19 እስከ 31 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የሀብት ኪሳራ እያጋጠማት መሆኑ፣ በቀይ ባሕር ላይ ያላትን ተሳትፎ ማሳደግ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ያረጋግጣል። የሽብር ቡድኖች ትስስርና የባዕዳን ኃይሎች መሠባሰብ በቀጣናው የሚፈጥሩት አለመረጋጋት፣ ኢትዮጵያ የራሷን የባሕር ኃይል መልሳ እንድታደራጅና የንግድ ኮሪደሮቿን የምታስከብርበትን ስትራቴጂ እንድትነድፍ አስገድዷታል።

ይህም ማለት የቀይ ባሕር የጸጥታ መታወክ ለኢትዮጵያ አስጊ ቢሆንም፣ የሀገራችንን የባሕር ኃይልና የዲፕሎማሲ አቅም በማሳደግ ረገድ እንደ ትልቅ መቀስቀሻ (Catalyst) ሊያገለግል ይችላል። በመሆኑም፣ በቀይ ባሕር አካባቢ የሚታየው የሽብር ቡድኖች ስርጭት፣ የኃያላን ሀገራት ወታደራዊ ክምችትና የጎረቤት ሀገራት አዲስ አሰላለፍ ኢትዮጵያን በስትራቴጂካዊ መስቀለኛ መንገድ ላይ አቁሟታል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ማዕበል ውስጥ በስኬት ለመውጣት የራሷን የኤሌክትሪክ ኃይልና የተፈጥሮ ሀብት እንደ መደራደሪያ የምትጠቀምበትና በቀጣናው የሚገኙ ኃይሎችን ወደ የጋራ ተጠቃሚነት የምታመጣበት የዲፕሎማሲ ጥበብ ጥቅም ላይ ታውላለች። የቀይ ባሕር ሞገድ ኢትዮጵያን አጥለቅልቆ የሚያጠፋ ሳይሆን፣ ወደ ላቀ የብልጽግና ደረጃ የሚያሸጋግራት "የትንሣኤ በር" የሚሆነው የጸጥታ ስጋቶችን ወደ ስትራቴጂካዊ ዕድል እየቀየረች በመሆኑ ነው። 130 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝቧን "ጂኦግራፊያዊ እስር ቤት" ለማውጣት የምታደርገው ጉዞም የሚሳለጠው፣ ይህንኑ የቀጣናውን የኃይል ሚዛንና የጸጥታ ውጥረት በብልህነትና በገለልተኝነት በመምራት ነው።

በአዶናይ ወልደአረጋይ