Search

የቀይ ባሕር ሕመም፡ የምጽዋ መስዋዕትነት እና የብ/ጄኔራል ተሾመ ተሰማ “የበር እና መስኮት” ኑዛዜ

እሑድ ሚያዝያ 18, 2018 278

የቀይ ባሕር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና፣ የታሪክ እና የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ እንደሚያነሱት ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ያላት ፍላጎት ሰላማዊ፣ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የሚፈታ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ዋና ዓላማ የታሪክ ስህተቶችን አርሞ ትውልድን ከየብስ እስረኝነት ማውጣት ነው። መንግሥት የቀይ ባሕር ጥያቄን እንደ ህልውና ጉዳይ በማንሳት ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ ማምጣቱ፣ የጄኔራል ተሾመ ተሰማንና በምጽዋ የወደቁትን ጀግኖች የታሪክ አደራ የመጠበቅ አካል ነው። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የ30 ዓመቱ ስህተት መታረም እንዳለበት የሚገልጹት፣ ይህንኑ በሤራ የተዘጋ “በርና መስኮት” በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመክፈት የሚደረገውን ጥረት ለማሳየት ነው። ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ያላት ታሪካዊ፣ ሕጋዊና ተፈጥሯዊ መብት በአንድ ጀምበር የጠፋ ሳይሆን፣ በውስጥና በውጭ ኃይሎች በታቀደ ሤራ እና በአመራር ድክመት ውጤት የመጣ መሆኑን የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ። 

ታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ “አይ ምዋ” በሚለው መጽሐፍ የሠራዊቱን ተጋድሎና የተሸረቡ ሤራዎችን የትውልድን ቁጭት በሚፈጥር መልኩ አቅረበዋል።   

የብርጋዴር ጄኔራል ተሾመ ተሰማ ማን ናቸው 

ብርጋዴር ጄኔራል ተሾመ ተሰማ በኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ታሪክ ውስጥ ሀገር ወዳድነታቸውና ወታደራዊ ጀግንነታቸው በደማቁ ከሚነሳላቸው ከፍተኛ መኮንኖች አንዱ ናቸው። በምዋ ውጊያ ወቅት የ6ኛ ነበልባል ክፍለ ጦር አዛዥ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፣ በወቅቱ ያሳዩት ጽናትና የወሰዱት የመጨረሻ እርምጃ ለኢትዮጵያ ሠራዊት ክብር ትልቅ ማሳያ ነው። ጄኔራሉ በጠላት እጅ ከመማረክ ይልቅ፣ በራሳቸው ሽጉጥ ሕይወታቸውን ማጥፋትን የመረጡት “የተመኘሁትን አገኘሁት” በማለት ነበር። መጽሐፉ ላይ እንደተጠቀሰው ጄኔራሉ ከተሰው በኋላ አስከሬናቸውን ለማግኘት የተደረገው ተጋድሎ ለጀግንነታቸው ማረጋገጫ እና ጄኔራሉ በሠራዊቱ ዘንድ የነበራቸውን ታላቅነትና ክብር ያሳያል።

በምጽዋ የተከፈለው መራር የደም ዋጋ 

የሀገራችን የባሕር በር ዕጣ ፈንታ የተወሰነውና ሠራዊቱ ለሉዓላዊነት መራር መስዋዕትነት የከፈለው በየካቲት 1982 ዓ.ም በምዋ ግንባር በተካሄደው ውጊያ ነው። በምጽዋ ግንባር የተካሄደው ውጊያ በኢትዮጵያ ወታደራዊ ታሪክ ውስጥ እጅግ ዘግናኝ ከሚባሉት አንዱ ነው። ታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ “አይ ምጽዋ” በሚለው መጽሐፍ የሠራዊቱን ተጋድሎና የተሸረቡ ሤራዎችን የትውልድን ቁጭት በሚፈጥር መልኩ አቅርበዋል።

ሠራዊቱ ለ240 ሰዓታት ያለ ማቋረጥ በከፍተኛ እልህ ተዋግቷል። ከተማዋ በመንገዶቿ ላይ በሬሳ የተሞላችና በደም ጎርፍ የታጠበች እንደነበረች የታሪክ ምሁራን ይመሰክራሉ። በተለይም የ6ኛ ነበልባል ክፍለ ጦር እና የ3ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር አባላት በምጽዋ ወደብ ላይ ያሳዩት ጽናት ለሀገር ድንበር መከበር የተከፈለ የደም ዋጋ ነበር። ደራሲው እንደገለጹት፣ ያ ግንባር “ሞት የተፈረደባቸው 17 ሺህ የኢትዮጵያ ሠራዊት” የተሰውበት ቦታ ነው።

ኢትዮጵያን ከባሕር ያገለላት ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ሤራ 

ወታደራዊ 

ኢትዮጵያ ከባሕር እንድትገለል የተደረገው በታሪክ ተጻራሪዎችና በወቅቱ በነበሩ የአመራር ውሳኔዎች መሆኑ ይገለጻል። በምጽዋ ግንባር የነበረው “መክት ዕዝ” የተከበበውና ከአሥመራ የሚመጣው የአቅርቦት መስመር የተቆረጠው በ1982 ዓ.ም ነበር። የአሥመራ-ምጽዋ መንገድ መቆረጥ ሠራዊቱን ለሁለት በመክፈል መከላከያ አቅሙን እንዲያጣ አድርጎታል። የዕዙ የበላይ ኃላፊዎች የአደጋውን ስፋት በሚገባ አለመረዳታቸውና የሚሰጡት ምላሽ የዘገየ መሆኑ ሠራዊቱን ለአስከፊ መስዋዕትነት ዳርጎታል። አንዳንድ ከፍተኛ መኮንኖችም ሕሊናቸው ሸፍቶ እንደነበርና ለሠራዊቱ ተገቢውን አመራር ባለመስጠት በሤራ ለጠላት አሳልፈው እንደሰጡት በመጽሐፉ ተጠቅሷል።

ዲፕሎማሲያዊ ሤራ 

የፖለቲካው ሤራ በወታደራዊ አመራር ላይ የፈጠረው ሤራ ቀጥሎ መጨረሻው ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር በመነጠል ነው የተጠናቀቀው። በተለይም በ1985 ዓ.ም የኤርትራን ነፃነት ተከትሎ፣ የዓሰብን ወደብ ለኢትዮጵያ የማስቀረት ዕድል እያለ በሤራና በቸልተኝነት እንዲወሰድ ተደርጓል። 

የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ የዚህ ድራማ ዋና ደራሲ፣ የኢትዮጵያ አመራሮች ደግሞ ተዋንያን እንደነበሩ ተደጋግሞ ተገልጿል። ይህ የኢትዮጵያ የወቅቱ አመራር ድራማ ተዋናይነት ያኔ በጦርነቱ ወቅት ተጀምሮ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትነጠል ተጠናቀቀ። ይህ ውሳኔ በምጽዋና በዓሰብ የፈሰሰውን የሠራዊቱን ደም ዋጋ ያሳጣ የታሪክ ስህተት ነበር።

“የትኛውም ሀገር ያለ በር እና መስኮት አይሠራም” 

የጄኔራል መኮንኑ ኑዛዜ ለዛሬው ትውልድ የተሰጠ አደራ ይመስላል። ብርጋዴር ጄኔራል ተሾመ ተሰማ “ለታሪክ ፀሐፊዎች” በተሰኘው ምዕራፍ ውስጥ፣ ሠራዊቱ እንዴት እንደተከዳ፣ በምን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንደተዋጋና የመጨረሻው መስዋዕትነት ለምን እንዳስፈለገ የሚገልጽ የታሪክ አደራ አስተላልፈዋል።

ጄኔራል ተሾመ ተሰማ ተናገሩት ተብሎ የሚጠቀሰው “የትኛውም ሀገር ያለ በር እና መስኮት አይሠራም” የሚለው አባባል፣ ዛሬ ኢትዮጵያ ካለችበት የባሕር በር ጥያቄ ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት አለው። ጄኔራሉ እንደገለጹት፣ የባሕር በር ለአንዲት ሀገር መግቢያ በር ነው።

የባሕር በር አለመኖር የኢኮኖሚ ነፃነትንና ሉዓላዊነትን ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ እንቅፋት መሆኑን ጄኔራሉ አስቀድመው ተመልክተውት ነበር።

ኢትዮጵያ ዛሬ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይዛ በዓመት እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር ለወደብ ኪራይ የምትከፍል መሆኗ፣ ሀገራችንን በኢኮኖሚ የየብስ እስረኛ አድርጓታል።

መስኮት ማለት ሀገራችን በዙሪያዋ ያለውን ቀጣና የምትቃኝበት፣ ብሔራዊ ደኅንነቷን የምትጠብቅበትና ስልታዊ ተፅዕኖዋን የምታሳርፍበት መሣሪያ ነው። ባሕር በር የሌላት ኢትዮጵያ በቀይ ባሕርና በኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ የሚከሰቱ ወታደራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን ለመከታተልና ለመቆጣጠር ትቸገራለች። አድማስ አቋርጠው የመጡ ሀገራት ደጇ ላያ ያሻቸውን የሚሆኑት መስኮቷ በሤራ ስለተዘጋ ነው። የጀግኖቿን አደራ የማትዘነጋዋ ኢትዮጵያ የባሕር ኃይልን መልሶ የማደራጀት ጥረቷ ይህንኑ “መስኮት” የመክፈት ጠረት አካል ነው።

የሠራዊቱ መስዋዕትነት በምጽዋ አሸዋ ላይ ፈስሶ እንዳይቀር፣ የባሕር በር ባለቤትነትን ማረጋገጥ ለዛሬው ትውልድ የተሰጠ የታሪክ ኃላፊነት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደሚያስገነዝቡት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን የረጅም ዘመን እጦት በሰላማዊ፣ በሕጋዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ጥበብ በታገዘ መንገድ ለመፍታት ቆርጦ ተነስቷል። ትናንት በጀግኖች መስዋዕትነት የታተመው የ“በር እና መስኮት” ጥያቄ፣ ዛሬ በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ብስለት የተሞላበት ውይይት ተፈትቶ፣ ኢትዮጵያ የነበረባትን የቀይ ባሕር ሕመም የምትፈውስበት ጊዜ አሁን ነው። 

በለሚ ታደሰ