ከ8 ቢሊዮን ብር ኪሳራ ወደ 2.1 ትሪሊዮን ብር ገቢ! የኢትዮጵያ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በዘጠኝ ወራት ውስጥ ያስመዘገቡት አስደናቂ ስኬት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ጉዞ ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሮታል። ይህ ለውጥ እንዴት ሊመጣ ቻለ?
የዚህ በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ሀገራችን ከተለመደው የኢኮኖሚ ዕድገት መግለጫዎች ባሻገር ጥልቅ የሆነ መዋቅራዊ እና የአሠራር ባህል ሽግግር ውስጥ መግባቷን የሚያረጋግጡ አዳዲስ ዕይታዎችን ይዟል።
የኢትዮጵያን የነገ ዕጣ ፈንታ የሚወስኑት የአመራር ግዳጅ (Leadership Duty) የተሰኘው አዲስ የሥራ ባህል፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከኪሳራ ወደ ትርፍ የተሸጋገሩበት የገቢ አውታር እና የፍትሕ ሥርዓቱን ወደ ዲጂታል የቀየረው "ስማርት ፖሊስ" ቴክኖሎጂ ተጠቃሾች ናቸው።

እነዚህ ስኬቶች ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካጋጠማት የዕዳ ጫና እና ቀውስ ወጥታ በሪፎርም አማካኝነት የ10.2 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ መዘጋጀቷን የሚያሳዩ ናቸው።
ከስኬቶቹ አንዱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ያስመዘገቡት አስደናቂ ትርፋማነት ነው። ባለፉት ዘጠኝ ወራት እነዚህ ድርጅቶች ከ8 ቢሊዮን ብር ኪሳራ ወጥተው 2.1 ትሪሊዮን ብር ገቢ ማስመዝገባቸው እና ለ96 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። ይህም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የመሠረተውን ሙያዊ የአመራር ሥርዓት ውጤታማነት ያረጋግጣል። ይህ ለውጥ ድርጅቶቹ ከመንግሥት በጀት ላይ ጥገኛ ከመሆን ወጥተው 600 ሚሊዮን ዶላር ታክስ እና 120 ሚሊዮን ዶላር የትርፍ ድርሻ ለመንግሥት ገቢ እንዲያበረክቱ አስችሏቸዋል።

በተለይም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻውን ከ2 ትሪሊዮን ብር በላይ የተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰቡና የ36 ቢሊዮን ብር የቅድመ ታክስ ትርፍ ማግኘቱ የፋይናንስ ዘርፉ የሀገራችን የኢኮኖሚ ሞተር እየሆነ መምጣቱን ያሳያል።
ሌላኛው ስኬት በከተማ ኮሪደር ልማት አማካኝነት የመጣው የሥራ ባህል ነው። ይህ አሠራር አመራሩ በሳምንት ሰባት ቀን እና በቀን 24 ሰዓት በሥራ ገበታው ላይ እንዲገኝ የሚያደርግ ሲሆን፣ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በጥራት እና በጊዜ እንዲጠናቀቁ አድርጓል።
ከዚህ ቀደም በተናጠል ሲሰሩ የነበሩት የኤሌክትሪክ፣ የውኃ እና የቴሌኮም መሠረተ ልማቶች አሁን በአንድ ማዕከል ተቀናጅተው እንዲታቀዱ መደረጉ የበጀት ብክነትን እና የጊዜ መዘግየትን ያስቀረ ትልቅ መዋቅራዊ ስኬት ነው።

ይህ የሰው-ተኮር የከተማ ልማት አቀራረብ ነዋሪዎችን ወደ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች በማሸጋገር እና የከተማ እንቅስቃሴን በማሻሻል ረገድ ለሌሎች የአፍሪካ ከተሞች አርአያ የሚሆን ነው።
በቴክኖሎጂው ዘርፍ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነውን "ስማርት ፖሊስ" ቴክኖሎጂን ተግባራዊ ማድረጓ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞዋን ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግሮታል።
ይህ ሲስተም ዜጎች በአካል ፖሊስ ጣቢያ ሳይገኙ ወንጀልን እና አደጋን በዲጂታል መንገድ እንዲያመለክቱ፣ ፋይላቸውን በስልካቸው እንዲከታተሉ እና ከአመራሮች ጋር በቀጥታ እንዲገናኙ ያስችላል።

በ"መሶብ" የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከ170 በላይ የመንግሥት አገልግሎቶች በዲጂታል መንገድ መሰጠታቸው ቢሮክራሲን በመቀነስ እና ግልጽነትን በማስፈን ረገድ የታየ ትልቅ ስኬት ነው።
ይህ የዲጂታል ዝላይ ከ"5 ሚሊዮን ኮደሮች" ሥልጠና ጋር ተዳምሮ የኢትዮጵያን ወጣቶች ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እያዘጋጀ ይገኛል።
በግብርናው ዘርፍ የታየው ስኬት ከምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ አርሶ አደሮችን ወደ ባለሀብትነት የሚያሸጋግር የ10 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፋ መደረጉ ነው።

ይህም ግብርናው ከባሕላዊ አሠራር ወጥቶ ወደ ገቢ-ተኮር (Agribusiness) እንዲሸጋገር የሚያደርግ ሲሆን፣ የስንዴ ኤክስፖርት እና የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብሮች ሀገራዊ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ያላቸውን ሚና አጠናክረው ቀጥለዋል።
እነዚህ ዘርፈ-ብዙ ስኬቶች እንደ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና የዓለም ገንዘብ ድርጀት ባሉት ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር ምስክርነትን ያገኘ ነው።
በዚህም በአራተኛው ዙር ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ግምገማ ስኬታማ እንድትሆን እና የ2.5 ቢሊዮን ዶላር የዕዳ እፎይታ እንድታገኝ በማድረግ ለኢኮኖሚ መረጋጋቱ ትልቅ መሠረት ጥለዋል።
በዓመቱ የሚመዘገበው የ10.2 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ኢትዮጵያን በአፍሪካ ፈጣን ዕድገት ካላቸው ሀገራት ተርታ ቀዳሚ አድርጓታል።
በለሚ ታደሰ