Search

ትናንትን በሽግግር ፍትሕ ማከም፤ ነገን በሀገራዊ ምክክር መገንባት

ሰኞ ሚያዝያ 19, 2018 326

የመደመር መንግሥት የፖለቲካ ዕሳቤ ትናንትን በሽግግር ፍትሕ የማረም፣ ነገን ደግሞ በሀገራዊ ምክክር የመገንባት ስትራቴጂን እንደ ትልቅ ምሰሶ ይጠቀማል።

ይህ አካሄድ ካለፈው ቁስል እየተፈወሱ፣ የወደፊቱን የጋራ ቤት በጠንካራ መሠረት ላይ ለመገንባት የሚያስችል ብልህ ስልት ነው።

ያለፉ በደሎች እና ግጭቶች ሳይታረሙ እና ተገቢው ፍትሕ ሳይሰጥ ወደ ፊት ለመጓዝ መሞከር "ቂምን አዝሎ እንደ መሮጥ" የሚቆጠር ሲሆን፣ የመሻገሪያው ድልድዮች ደግሞ የሽግግር ፍትሕ እና ሀገራዊ ምክክር ናቸው።

የሽግግር ፍትሕ ያለፈውን ሸክም የሚያቀልል ሲሆን፣ ሀገራዊ ምክክር ደግሞ የነገውን መንገድ የሚጠርግ በመሆኑ ሁለቱ ሂደቶች የማይነጣጠሉ እና ተመጋጋቢ የሰላም መሣሪያዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ የበርካታ ማንነቶች፣ ጥንታዊ እሴቶች እና የጋራ ታሪክ ባለቤት ብትሆንም፣ ባለፉት ዘመናት የተፈጠሩ ግጭቶች እና የተቀነቀኑ የበደል ትርክቶች ለሀገረ መንግሥት ግንባታው እና ለዘላቂ ሰላሙ ፈተና ሆነው ቆይተዋል።

የመደመር መንግሥት እነዚህን ታሪካዊ እና መዋቅራዊ ስብራቶች ለመጠገን "ትናንትን በሽግግር ፍትሕ፤ ነገን በሀገራዊ ምክክር" የማከም ጽኑ አቋም ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ይህም የነገው መሠረት መገንባት ያለበት በበቀል ላይ ሳይሆን በእውነት፣ በፍትሕ እና በዕርቅ ላይ መሆን እንዳለበት ከሚሰጠው እምነት የሚመነጭ ነው።

የቂም በቀል አዙሪትን የሚሰብረው የሽግግር ፍትሕ

ያለፉ በደሎችን በዝምታ ማለፍ ቂምን ማምረት በመሆኑ፣ የወንጀል ተጠያቂነትን፣ እውነትን ማውጣትን፣ ምሕረትን፣ ካሣን እና ተቋማዊ ሪፎርምን ያካተተ ሀገር በቀል የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት መዘርጋት የግድ ይላል።

ትናንትን በሽግግር ፍትሕ ማከም ማለት ባለፉት ዓመታት የታመቁ ቁስሎችን እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በግልጽ አውጥቶ በመወያየት ለዘላቂ ሰላም መሠረት መጣል ማለት ነው።

የሂደቱ ዋና ዓላማ የቂም በቀልን አዙሪት ሰብሮ፣ ማኅበራዊ ትሥሥርን ማደስ እና ዜጎች በመንግሥት ተቋማት ላይ ያላቸውን እምነት የበለጠ እንዲገነቡ ማድረግ ነው። ያለፈውን ታሪክ በፍትሕ ሚዛን ሳንቃኘው ወደ ፊት መራመድ ስለማይቻል፣ የሽግግር ፍትሕ ለሀገራዊ መረጋጋት ወሳኝ ቅድመ-ሁኔታ ነው።

ሀገራዊ ምክክር፡ አካታችነት እውን የሚሆንበት የሠለጠነ መንገድ

በተጨማሪም ልዩነቶች በጠረጴዛ ዙሪያ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ እና አዲስ የፖለቲካ ባህል እንዲገነባ ብቸኛው መንገድ ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ምክክር ነው።

ነገን በሀገራዊ ምክክር መቃኘት ማለት በኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቁ እና ለልዩነት ምክንያት የሆኑ መሠረታዊ የፖለቲካ እና የታሪክ ጉዳዮችን በውይይት እና በሐሳብ የበላይነት መፍታት ማለት ነው።

በዚህ ሂደት በጋራ እሴቶች፣ በሕገ-መንግሥታዊ ጉዳዮች እና በሀገረ-መንግሥት ግንባታ ላይ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ይቻላል።

ይህም ማንም የማይገለልባት እና የሁላችንም የሆነች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያስችል የሠለጠነ መንገድ ነው።

የተጀመረው ዴሞክራሲያዊ ባህልን የመገንባት ተስፋ ሰጪ ጉዞ

የመደመር መንግሥት ይህንን ዴሞክራሲያዊ ባህል ለማስፈን ረጅም ርቀት ተጉዟል። በገለልተኛ ባለሙያዎች የተመራ እና ሦስት ሺህ በላይ ዜጎች የተሳተፉበት፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮን ከሀገር በቀል እውነት ጋር ያቀናጀ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ፀድቆ ወደ ትግበራ እየገባ ይገኛል።

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተፈጠረውን ግጭት በፕሪቶሪያ ስምምነት በሰላም ከመቋጨት ባለፈ፣ በሌሎች አካባቢዎች ያሉ የታጠቁ ቡድኖችም ወደ ሰላም እንዲመጡ ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ ነው።

የፍትሕ እና የዳኝነት ተቋማት ከፖለቲካ ተጽዕኖ ነጻ ሆነው የዜጎችን እኩልነት እንዲያረጋግጡ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎችም ለውጥ እያመጡ ነው።

በተጨባጭ የታዩ ስኬቶችም የመንግሥትን ቁርጠኝነት ያሳያሉ። በቀድሞው የደቡብ ክልል ለዘመናት የቆዩ የማንነት እና የአደረጃጀት ጥያቄዎች በሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ምላሽ ማግኘታቸው ለአካባቢው አንጻራዊ ሰላም እና ልማት ምክንያት ሆኗል።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ግጭቶች እና አለመግባባቶች በሀገር በቀል የሽግግር ፍትሕ እና በሀገር ሽማግሌዎች ጥረት መፍትሔ አግኝተዋል። በተጨማሪም የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ተካትተው እንዲሠሩ በማድረግ የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስፋት ተችሏል።

ወደፊትም የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን ወደ ሙሉ ትግበራ በማስገባት ተጎጂዎች ካሣ የሚያገኙበት፣ እውነት የሚወጣበት እና አጥፊዎች ተጠያቂ የሚሆኑበት ሥርዓት ይረጋገጣል።

የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን በስኬት በማጠናቀቅም አወዛጋቢ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ ስምምነት ላይ ይደረሳል።

ሙስናን እና ሕዝባዊ እንግልትን ከመሠረቱ የሚነቅል፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ እና ለዜጎች ደኅንነት ቅድሚያ የሚሰጥ ጠንካራ ሲቪል ሰርቪስ እየተገነባ ነው።

የሰላም እና የአንድነት እሴቶችን በትምህርት ሥርዓት ውስጥ በማካተትም ከቂም እና ከጥላቻ የጸዳ አዲስ ትውልድ ለመፍጠር በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።

ባለፉት ዓመታት ያሳለፍናቸው ግጭቶች እና በግጭቶቹ መሐል የተፈጠሩ የመብት ጥሰቶች በዜጎቻችን ላይ ያደረሱት ስቃይ በዝምታ የሚታለፍ አይደለም። ነገር ግን ቁስላችን የሚድነው በበቀል ሳይሆን በእውነት እና በፍትሕ ነው።

የጀመርነው የሽግግር ፍትሕ ሂደት ዓላማው ግልጽ ነው፤ በደል አድራሾች ኃላፊነት እንዲወስዱ፣ ተጎጂዎች ዕውቅና እና ካሣ እንዲያገኙ፣ እንዲሁም ዳግመኛ በደል የማይፈጸምባቸው ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ነው።

የነገዋ ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በዛሬው ምክክራችን ነው። ልዩነቶቻችንን በጠመንጃ ሳይሆን በሐሳብ የምንፈታበት አዲስ ብሔራዊ ቃል-ኪዳን የምንገባበት ወቅት ላይ እንገኛለን።

ቂም እና ቁርሾን ለትናንት ትተን፣ በፍቅር እና በውይይት የምትመራ፣ ለልጆቻችን የምትመች እና በሁለንተናዊ ብልጽግና የደመቀች ኢትዮጵያን መገንባት ለነገ የማይባል የትውልዱ የቤት ሥራ ነው።

በበረከት ሽመልስ