የአሰብ ወደብ እና የኢትዮጵያ ቁርኝት ለዘመናት የኖረ እና በቀላሉ የማይበጠስ የታሪክ ሥር ያለው ነው። በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ፣ የጣሊያኑ ሩባቲኖ ኩባንያ የአካባቢውን ሱልጣኖች በማታለል በ6 ሺህ ማሪያ ቴሬዛ አሰብን ሲገዛ፣ የኢትዮጵያ ነገሥታት ፈቃድም ሆነ እውቅና አልነበረውም።
ይህ በ1862 ዓ.ም የተጀመረው "የንግድ ሽያጭ"፣ በኋላ ላይ ጣሊያን ለፈጸመችው የቅኝ ግዛት ወረራ መከፈቻ ሆነ። ጣሊያን በ1900ዎቹ መጀመሪያ ላይ በወታደራዊ ጫና ያስፈረመቻቸው የድንበር ውሎች፣ በዓለም አቀፍ የውል ስምምነት ሕግ (Vienna Convention) መሠረት በግዳጅ የተፈጸሙ በመሆናቸው ዛሬም ድረስ በሕግ ፊት ፅኑ መሠረት የላቸውም።
ፋሺስት ጣሊያን በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት እነዚህን ውሎች ሁሉ በግብር አፍርሳቸዋለች። ታሪክ እንደሚነግረን፣ አሰብ በሕግም ሆነ በተፈጥሮ የኢትዮጵያ እንጂ የማንም ባዕድ አካል ሆና አታውቅም።
ወደ ቅርብ ታሪካችን ስንመለስ፣ የደርግ ዘመነ መንግሥት ለአሰብ ወደብ የሰጠው ስትራቴጂያዊ ትኩረት ሊጠቀስ የሚገባው ነው። ደርግ አሰብን "ሁለተኛዋ የአዲስ አበባ መዝጊያ" በማለት ይጠራት ነበር። ይህ ስያሜ በዘፈቀደ የወጣ ሳይሆን፣ ወደቧ ለኢትዮጵያ ያላትን ወሳኝ ፋይዳ በሚገባ ከተረዳ አመራር የመነጨ ነበር። በሶቪየት ኅብረት እና በዩጎዝላቪያ ቴክኒካዊ ድጋፍ፣ አሰብ በምሥራቅ አፍሪካ ተወዳዳሪ የሌላት ዘመናዊ የወደብ መሠረተ ልማት ባለቤት እንድትሆን ተደርጓል። ትላልቅ መርከቦችን የሚያስተናግዱ ጥልቅ የባሕር በርቶች፣ ግዙፍ ክሬኖች እና የመጋዘን ሥርዓቶች የተገነቡት በዚሁ ዘመን ነበር።
ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ አሰብ የኢትዮጵያ የኃይል ዋስትና ማዕከል ነበረች። በሩሲያ መሐንዲሶች የተገነባው የ"ዜን" የነዳጅ ማጣሪያ ተቋም፣ ሀገራችን ድፍድፍ ነዳጅን በርካሽ አስገብታ እንድታጣራ እና የውጭ ምንዛሬ እንድትቆጥብ አስችሏታል።
ዛሬ ላይ የኢነርጂ ጥገኝነት ለሚያሰቃየን ኢትዮጵያውያን፣ የአሰብ ማጣሪያ ታሪክ ትልቅ ቁጭትን ይጭራል። ደርግ በ1980 ዓ.ም አሰብን ከኤርትራ ክፍለ ሀገር አስተዳደር ነጥሎ "የአሰብ ራስ-ገዝ መስተዳድር" ማድረጉ፣ ወደፊት ሊመጣ የሚችለውን የጂኦ-ፖለቲካዊ አደጋ አስቀድሞ ለመከላከል የተደረገ ስትራቴጂያዊ እርምጃ ነበር። ይህ እርምጃ የአፋር ሕዝብን ጥያቄ ከመመለሱም በላይ፣ ወደቡ በቀጥታ በማዕከላዊ መንግሥት ሥር እንዲጠበቅ አድርጓል።
ሆኖም በ1983 ዓ.ም የመጣው የፖለቲካ ሽግግር፣ ይህንን ሁሉ አኩሪ ስኬት ወደ አመድነት ቀየረው። የወቅቱ አመራር በወቅቱ የወሰደው አቋም፣ የሀገራችንን ሉዓላዊ ግዛት አሳልፎ ከመስጠት ባለፈ፣ የባሕር በርን እንደ ቅንጦት በመቁጠር የታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት ፈጽሟል።
የሽግግር መንግሥቱ የሀገርን ድንበር የመቀየር ሕገ-መንግሥታዊ ሥልጣን ሳይኖረው፣ አሰብን ለኤርትራ አሳልፎ መስጠቱ ዛሬም ድረስ በታሪክ ክህደትነት የሚወቀስ ተግባር ነው።
ከጦርነቱ በኋላ የተደረገው የአልጄርስ ስምምነትም ቢሆን፣ በፍትሐዊነት ላይ ሳይሆን በቅኝ ግዛት ውሎች ላይ ብቻ ተመሥርቶ በመወሰኑ፣ የኢትዮጵያን የባሕር በር መብት እንደገና የቀበረ ውሳኔ ሆኖ ተመዝግቧል።
ዛሬ ኢትዮጵያ የባሕር በር በማጣቷ የምትከፍለው ዋጋ እጅግ ዘግናኝ ነው። በየዓመቱ እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር ለጅቡቲ ወደብ ኪራይ የምናፈሰው ሀብት፣ ለትምህርት ቤቶች፣ ለሆስፒታሎች እና ለግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ሊውል የሚችል ነበር።
የነዳጅ፣ የማዳበሪያ እና የመድኃኒት ዋጋ በወደብ ኪራይ ምክንያት መናሩ በዜጎቻችን ኑሮ ላይ የፈጠረው ጫና ቀላል አይደለም።
ከኢኮኖሚው ባለፈ፣ የባሕር ኃይላችንን ማጣታችን እና በቀይ ባሕር ላይ ያለን ተፅዕኖ መቀነሱ፣ ብሔራዊ ደኅንነታችንን ለከፍተኛ ስጋት አጋልጦታል።
130 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት እና ግዙፍ ኢኮኖሚ እየገነባች ያለች ሀገር፣ በአንድ ወደብ ላይ ብቻ ጥገኛ መሆኗ እብደት ነው።
የአሰብ ጉዳይ ሲነሣ ከአፋር ሕዝብ ማንነት ጋር ያለውን ጥልቅ ትሥሥር መዘንጋት አይቻልም። የአፋር ሕዝብ አሰብን እንደ ተፈጥሮ የባሕር በሩ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ኢትዮጵያዊ ማንነቱ መገለጫ አድርጎ ይቆጥራታል።
የባሕር በሩ መታጣት የአፋርን ሕዝብ ለሁለት ከመክፈሉም በላይ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትሥሥሩን አቃውሶታል። አሰብ ለኢትዮጵያ መመለስ ማለት፣ ለዚህ ታማኝ ሕዝብ ፍትሕ መመለስ ማለት ነው።
አሁን ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት የባሕር በር ጥያቄን እንደገ እና የብሔራዊ አጀንዳ አድርጎ ማንሳቱ አዲስ የተስፋ ብርሃን ፈንጥቋል። ይህ ጥያቄ የጦርነት ጉሰማ ሳይሆን የሕልውና ጥያቄ ነው።
አሰብን በሰላማዊ፣ በሕጋዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማግኘት የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ቢሆን፣ ግዙፏ ኢትዮጵያ ያለ ባሕር በር መኖሯ ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ስጋት መሆኑን ተረድቶ፣ ለፍትሐዊ መፍትሔ ትብብር ሊያደርግ ይገባል።
አሰብ የኢትዮጵያ የታሪክ ርስት፣ የኢኮኖሚ ዋስትና የደኅንነት ጋሻዋ ነው። ባለፉት ስምንት ዓመታት የተጀመረው የሪፎርም ጉዞ፣ ይህንን የታሪክ ስብራት ጠግኖ ኢትዮጵያን ወደ ቀድሞ ልዕልናዋ የመመለስ ግዴታ አለበት።
የባሕር በር ባለቤትነት ለኢትዮጵያ የቅንጦት ጥያቄ ሳይሆን፣ የኢኮኖሚ ነፃነት እና የብሔራዊ ደኅንነት ዋስትና ነው።
የታሪክ ስህተቶችን በማረም፣ አሰብ እንደገና የኢትዮጵያ የሰላም እና የልማት ደጃፍ የምትሆንበትን ጊዜን እንጠብቃለን። ይህ የትውልድ አደራ ነው፤ ይህ የሕልውና ጥያቄ ነው!
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ