የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ሽግግር ሀገራዊ ሉዓላዊነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ምሶሶ መሆኑን የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገልጿል።
መንግሥት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን የሉዓላዊነት ልብ አድርጎ መቅረጹን አመልክቷል።ይህም መሠረታዊ ፍላጎቶችን በራስ አቅም ለመሸፈንና ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ ነፃነትን ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን ጠቁሟል።
ይህ መዋቅራዊ ሽግግር ተግዳሮቶችን ወደ ስትራቴጂካዊ ድል በመቀየር ላይ እንደሚገኝም አገልግሎቱ ገልጿል።
የጀመረው ግዙፍ ሽግግር አሁን ላይ ወደ ላቀ የቴክኖሎጂ ባለቤትነት ምዕራፍ መሸጋገሩን አመልክቶ፤ይህም መንግሥት ዘርፉን ለማላቅ ያለውን ጠንካራ አቋም የሚያሳይ መሆኑን ጠቁሟል።
በሐዋሳ፣ በደብረብርሃንና በአዲስ አበባ ወደ ሥራ የገቡት የሶላር ሴል ማምረቻ ፋብሪካዎች ለዚህ ማሳያ መሆናቸውንም ገልጿል። ፋብሪካዎቹ በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ላይ እንደሚገኙም ጠቁሟል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት አቅጣጫ ከመሠረቱ መቀየሩን የገለጸው አገልግሎቱ፤ መንግሥት ከብዛት ወደ ስልታዊ ጥራት የሚያመራ አዲስ ፖሊሲ ነድፎ ወደ ተግባር መግባቱን ጠቅሷል።
ይህም ወጣቱን የቴክኖሎጂ ባለቤት እንደሚያደርገው በማመልከት፣ ከዚህም በተጨማሪ የ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ የገቢ ምርት ጥገኝነትን በከፍተኛ ፍጥነት እየቀነሰ መሆኑን ገልጿል።
እንደ ብረት ማዕድንና ማርብል ያሉ ሀብቶችን ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት በማድረግ የውጭ ምንዛሬን መታደግ መቻሉንም ጠቁሟል።
መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ልዩ ትኩረት ተዘግተው የነበሩ ከ800 በላይ ፋብሪካዎችን ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማስቻሉ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም አጠቃላይ የማምረት አቅምን ወደ 67 በመቶ ከፍ ማድረግ እንዳስቻለ ተጠቅሷል።
የኢንዱስትሪ ዕድገቱ ለረጅም ጊዜ ብልጽግና የተጣለውን መሠረት ፍሬ ማፍራት መጀመሩን እንደሚያሳይ ያመለከተው አገልግሎቱ፣ ኢትዮጵያ ዛሬ የቆመችበት ጽኑ መሠረትም ነገን በልበ ሙሉነት ለመቀበል የሚያስችል ብሩህ የታሪክ ምዕራፍ መሆኑን ጠቁሟል።