የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 17ኛ መደበኛ ስብሰባ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ መካከል የተፈረመውን የ80 ሚሊዮን ዩሮ የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅ መርምሮ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።
የብድር ስምምነቱን አስፈላጊነት አስመልክተው የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ ምህረቱ ሻንቆ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፤ ድጋፉ መንግሥት የጀመረውን የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕቅድ ለማገዝ የታለመ የቀላል ብድር መሆኑን አስረድተዋል።
ብድሩ በቀጥታ ወደ መንግሥት ግምጃ ቤት የሚፈስ ሲሆን፣ መንግሥት እያከናወነ ያለውን ስር ነቀል የኢኮኖሚ ለውጥ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የኢነርጂ ዘርፍ እንቅስቃሴዎችን ለማጠናከር የሚውል መሆኑም ተመላክቷል።
ይህ የፋይናንስ ድጋፍ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥና የመንግሥትን የበጀት አቅም ለማጎልበት ታስቦ የቀረበ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰዋል፡፡
የብድር ስምምነቱ በዓመት 1.1 በመቶ ዝቅተኛ ወለድ የሚታሰብበት፣ 0.5 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ የሚፈጸምበት እና የ5 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ15 ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ መሆኑንም መግለጻቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል።
ምክር ቤቱም የብድር ስምምነቱ ከኢትዮጵያ የብድር ስትራቴጂ ጋር የተጣጣመና በክፍያ ረገድ ጫና የማይፈጥር በመሆኑ እና መንግሥት የገቢ አሰባሰብን ለማሳደግ፣ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋትና መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የጀመረውን ጥረት ይበልጥ እንደሚያግዘው በማንሳት ረቂቅ አዋጁን አዋጅ ቁጥር 1414/2018 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡