Search

የኢራን እና የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ባለስልጣናት ውይይት

Aug 12, 2025

የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ከፍተኛ ባለስልጣን ከኢራን ባለስልጣናት ጋር ተወያዩ።

የኢራን ብሔራዊ ሚዲያ እንደዘገበው፤ ውይይቱ ኢራን በሰኔ ወር ከኤጀንሲው ጋር ትብብሯን ካቋረጠች በኋላ የተደረገ የመጀመሪያው የከፍተኛ ባለስልጣናት ውይይት ነው

የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ማሲሞ አፓሮ ከኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣናት እና ከኒውክሌር ባለስልጣናት ጋር ተወያይተዋል።

ቴህራን ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ጋር ትብብሯን ለማቆም መወሰኗን ተከትሎ፤ በቀጣይ ከተቋሙ ጋር ኢራን ስለሚኖራት የትብብር ማዕቀፍ ዙሪያ ያተኮረ መሆኑን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዜም ጋሪባባዲ ለኢራን የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቀጣይም ሁለቱ ወገኖች በተከታታይ ምክክር ለማድረግ መስማማታቸውንም ተናግረዋል።

አክለውም ኢራን በኒውክሌር ተቋማቷ ላይ የደረሰባትን ጥቃት ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ማለፉ ተገቢ አይደለም ያሉ ሲሆን፤ ኤጀንሲው የኒውክሌር መርሐ ግብሮችን በሚመለከት የሚከተላቸው አካሄዶች ላይ ለውጥ እንዲደረግ ጠይቀናልም ብለዋል።

በሰኔ ወር መገባደጃ ላይ የኢራን ፓርላማ ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ጋር ያለውን ትብብር የሚያቋርጥ ውሳኔ አሳልፎ እንደነበር ይታወሳል።