ባሕርዛፍ ባለው ጠቀሜታ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ቢሆንም፣ በሀገር በቀል እፅዋት እድገትና ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑ ይታመናል፡፡
በተለይ ባሕርዛፍን የእርሻ ማሳ አካባቢ መትከል ምርትና ምርታማነት ከመቀነስ ባለፈ በዘላቂነት የአፈር ጉዳትን ያስከትላል፡፡
የባሕርዛፍ ሥር ከ30 ሜትር በላይ በጥልቀት ወደ ታችም ሆነ ወደ ጎን የማደግ አቅም ስላለው የከርሰ ምድር ውኃ መጠንን ይቀንሳል፤ በዚህም አፈር በቂ እርጥበት እንዳይኖረው ያደርጋል፡፡
በአፈር ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮችንም በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ ለምነትን ያሳጣል፡፡
ባሕርዛፍ በአካባቢው የሚገኙ ሰብሎችና እፅዋቶች በቂ የፀሐይ ብርሃን እንዳያገኙ ከመከለል ባለፈ፣ ምግብ በመሻማት በቂ ምርት በወቅቱ እንዳይሰጡ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡
በመሆኑም የባሕር ዛፍን አሉታዊ ተጽዕኖ ከግምት ውስጥ በማስገባት ባሕርዛፍ ተመንጥሮ ለምግብነት በሚውሉና ከፍተኛ ጠቀሜታ ባላቸው እንደ ቡና፣ አቮካዶ፣ ሙዝ በመሳሰሉት የመተካቱ ተግባር በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተለመደ መጥቷል፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀላባ ዞን አርሶ አደሮችም በማሳቸው ላይ የነበረን ባሕርዛፍ በመመንጠር ቡና በመትከል ተጠቃሚ ሆነናል ሲሉ ለኢትዮጵያ ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሮቹ ቡናን በመትከል በአጭር ጊዜ ምርታማ መሆን በመቻላቸው ገቢያቸውን ማሳደግ እና ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡
ከዚህ ቀደም በባሕር ዛፍ ተሸፍኖ የነበረውን መሬት ወደ ቡና የመቀየር ዘመቻ ተጀምሯል ያለው የዞኑ ግብርና መምሪያ፣ በሚቀጥሉት ዓመታት የዞኑን የቡና ሽፋን ወደ 20 ሺህ ሄክታር ለማሳደግ መታቀዱንም አስታውቋል፡፡
በእንቻለው አያሌው