Search

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚወግነው ለሀገር ብቻ ነው - ፕሮፌሰር መስፍን ዓርዓያ

ማክሰኞ ነሐሴ 06, 2017 114

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚወግነው ለሀገር እና ለሕገ-መንግስት ብቻ መሆኑን፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽር ፕሮፌሰር መስፍን ዓርዓያ ገለጹ።

ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም ከሁሉም ሰው የተሰበሰቡ ሃሳቦች በጋራ ተነጥረው በወጡት ላይ እንመክራለንም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በትግራይ ክልል እና በዳያስፖራው ማኅበረሰብ አካባቢ አጀንዳ ለመሰብሰብ እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥቷል።

ማብራሪያውን የሰጡት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን ዓርዓያ እንደገለፁት፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ወደትግራይ ክልል ሥራዎቹን ለማከናወን ዝግጅቱን በመጨረስ ላይ ይገኛል።

ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ ጋርም የምክክር ሥራዎች መጀመራጀውን አንስተው፤ በውጭ ሀገራት የሚደረገው ምክክርም እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጊዜ እና ገንዘብን ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ በይነ መረብን ዋናው የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መንገድ ማድረጉንም ገልፀዋል።

በዚህም በቅርቡ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በተደረገ የበይነ መረብ ግንኙነት ብዙ አጀንዳዎች መሰብሰባቸውን አንስተዋል።

በተጨማሪምአውሮፓ፣ እስያ፣ ትራንስ አትላንቲክ እና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን በሚገኙባቸው አካባቢዎች በበይነ መረብ አጀንዳ ማሰባሰብ ይደረጋል ነው ያሉት።

ከዚህ ባሻገር ተምሳሌታዊ በሆነ መልኩ በተወሰኑ ቦታዎች ኮሚሽነሮች በገፅ ለገፅ ግንኙነት አጀንዳወችን መሰብሰብ መጀመራቸውን ገልፀዋል።

የመጀመሪያውደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ላይ እየተደረገ የሚገኘው ሲሆን፤ተመሳሳይ በአሜሪካ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋርም ኮሚሽነሮች በገፅ ለገፅ ግንኙነት አጀንዳወች እንዲሰበሰቡ እንደሚደረግም አንስተዋል።

በዋሽንግተን ዲሲ ከሁለት ሳምንት በኋላ ኮሚሽነሮች ተገኝተው አጀንዳ እንደሚያሰባሰቡ እና በቀጣይ ደግሞ በካናዳ በዩናይትድ ኪንግደም እንዲሁም በስዊድን አጀንዳዎችንመሰብሰብ ሥራዎች እንደሚካሄዱም ጠቁመዋል ዋና ኮሚሽነሩ።

በዚህ ሂደት ተሰብሰበው እና ምክክር ተደርጎባቸው መግባባት ላይ የተደረሰባቸው አጀንዳዎች፤ ወደ ተግባሪ አካላት የሚተላለፉ ይሆናልም ብለዋል።

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ደግሞ ሥራዎችን በመከታተል ተግባራዊ መሆናቸውን ለሕዝብ ያሳውቃልም ነው ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ።

በሴራን ታደሰ