Search

ኢትዮጵያ ከዳር ተመልካችነት ወደ ቀዳሚዋ አፍሪካዊት ኃይል

ሓሙስ ግንቦት 06, 2018 379

ኢትዮጵያ ለዘመናት በዓለም አቀፉ ሥርዓት ውስጥ  የተከታይነት ተጽዕኖ ጥላ ሥር መቆየቷ ይታወሳል። ይህ ሁኔታ የሌሎችን በጎ ፈቃድ ጠባቂ፣ በገዛ ተፈጥሮአዊ ሀብቷ እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የዳር ተመልካች አድርጓት ቆይቷል።
ይሁን እንጂ የመደመር መንግሥት ይህ የታሪክ ጠባሳ የሚያበቃበት ጊዜ አሁን ነው በሚል ጽኑ እምነት ወደ ተግባር ከገባ ሰንብቷል። ሀገራችን ያላትን ጥንታዊ ታሪክ፣ ድንቅ ባህል፣ የተፈጥሮ ጸጋና የሰው ኃይል በአግባቡ በመጠቀም፣ ከቀጠናዊ ተጽዕኖ ባለፈ ዓለም አቀፍ ተደማጭነት ያላት አፍሪካዊት ኃይል የመሆን ራዕይ ሰንቃለች።
ይህ ራዕይ የተገነባው በተለመዱት የኃይል ሚዛን መንገዶች ሳይሆን በሁለንተናዊ ብልፅግና፣ በጋራ ተጠቃሚነትና በአዎንታዊ ገንቢ ኃይልነት ላይ ነው። 

የመደመር ዕሳቤ ኢትዮጵያን ከዳር ተመልካችነት ወደ መሪነት ማሸጋገር ሲሆን ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሀገራችን የዲፕሎማሲ አድማሷን በማስፋት፣ እንደ ብሪክስ (BRICS) ያሉ ዓለም አቀፍ ስብስቦችን በመቀላቀልና የደቡብ-ደቡብ ትብብርን በማጠናከር ብሔራዊ ጥቅሟን በላቀ ደረጃ አስከብራለች። 

ኢትዮጵያን "አፍሪካዊት ኃይል" የማድረግ ሕልም የበላይነትን በመጫን ላይ የተመሠረተ ሳይሆን ትርጉሙ አዎንታዊና ገንቢ ኃይል መሆን ነው። ይህም በቅንነት፣ በወንድማማችነትና በፍትሕ ላይ የተመሠረተ የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ፣ ከአጎራባች ሀገራት ጋር ያለውን ስትራቴጂያዊና መሠረተ ልማታዊ ትስስር ማጠናከር እንዲሁም በምግብ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠችና የዜጎቿን ክብር ያስጠበቀች ሀገር መገንባትን ያካትታል። ይህ በወረቀት ላይ የሰፈረ ምኞት ብቻ ሳይሆን  ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተጨባጭ መሠረቶች የተጣሉበት ተግባር ነው። 

በዓለም አቀፍ መድረኮች የድምፅ ባለቤትነታችንን ከማረጋገጥ ጀምሮ በኤሌክትሪክ ኃይል፣ በባቡርና በመንገድ ትስስር የምሥራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማዕከል ለመሆን የሚያስችሉ ግዙፍ ሥራዎች ተከናውነዋል።

በቅርቡ የአፍሪካ ኅብረት ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና የዲጂታል ጤና ሻምፒዮን አድርጎ መሾሙ እንዲሁም ቀደም ሲል የተቀበሏቸው የFAO የአግሪኮላ ሜዳሊያ እና የላቀ የአፍሪካ መሪነት ሽልማቶች የኢትዮጵያ ስኬት ዓለም አቀፋዊ ምስክሮች ናቸው። 
መንግሥት ኢትዮጵያን ዘግይቶ ከመድረስ ዕዳ ወደ ቀድሞ መድረስ በረከት ለማሸጋገር በተቀመጠው ርዕይ መሠረት፣ በፈጠራና ቴክኖሎጂ ግንባር ቀደም ለመሆን ደፋር እርምጃዎችን ወስዷል።
የአፍሪካን የመጀመሪያውን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት በመመሥረትና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በዲጂታል የክፍያ ሥርዓቶች በማሳለጥ ቢሮክራሲያዊ እንቅፋቶችን መቅረፍ ተችሏል። 

በአካባቢ ጥበቃ ረገድም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረ ወዲህ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች በመተከላቸው የደን ሽፋናችን ወደ 23 በመቶ አድጓል። ይህ ስኬት ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ተሟጋችነት ከተሳታፊነት ወደ መሪነት ከፍ አድርጓታል። 
በግብርናው ዘርፍም በስንዴ በምግብ ሉዓላዊነት መርሃ ግብር አማካኝነት በ2010 ዓ.ም ከነበረበት 27 ሚሊዮን ኩንታል በ2017 ዓ.ም ወደ 280 ሚሊዮን ኩንታል ማደጉ ኢትዮጵያ በስንዴ ራሷን እንድትችል አድርጓታል። 

ዩኒቨርሲቲዎቻችንንና የምርምር ተቋሞቻችንን የሥልጣኔና የኢኖቬሽን ማዕከል ማድረግ ቀጣዩ የቤት ስራችን ነው። በምግብ ራሳችንን ከመቻል አልፈን፣ የቀጣናው የኢንዱስትሪና የንግድ ማዕከል በመሆን የዜጎችን የነፍስ ወከፍ ገቢ ማሳደግ ትልቁ ግባችን ነው።

ኢትዮጵያን አፍሪካዊት ኃይል አድርጎ የመገንባት ሕልም የሩቅ ምኞት ሳይሆን አሁን በላባችን እየተገነባ ያለ እውነታ ነው። ይህ ጉዞ የሁላችንም ነው። የኢትዮጵያ ብልፅግና ለሌሎች የተስፋ ብርሃን የሚሆን፣ በአዎንታዊ ዕሴቶች ላይ የተመሠረተና አብሮ በማደግ የሚያምን ይሆናል፡፡

በትላንት ታሪክ ታንጸን፣ በዛሬ ጥረት በርትተን፣ ለነገዋ ኃያል ኢትዮጵያ መትጋት የትውልዱ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው። በደም መስዋዕትነት የተረከብናትን ሀገር በላብ በማፅናት፣ አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ ጉዞ የሁላችንንም ቁርጠኝነት ይጠይቃል።

 

በአዶኒያስ ወ/አረጋይ