ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተምሳሌት በመሆን የፓን-አፍሪካኒዝም እሳቤ ተፈጥሯዊ ጉልበት ሆና ቆይታለች።
አውሮፓውያን አህጉሪቱን ለመቀራመት ሲነሡ፣ ኢትዮጵያ በከፍታ ላይ የቆመች እና ሥልጣኔን ያጣጣመች ዕድሜ ጠገብ ሀገር ናት።
ታሪካዊው የዓድዋ ድል እስከ አፍንጫው ታጥቆ የመጣውን የቀኝ ገዢ ኃይል በማንበርከክ የነጭ የበላይነትን እሳቤ ገልብጧል፤ የዓድዋ ድል ለፓን-አፍሪካኒዝም ንቅናቄ አዲስ ጉልበትና የይቻላል መንፈስን አጎናጽፏል።
የትናንቱ የፓን-አፍሪካኒዝም ትግል ማዕከል የፖለቲካ ነጻነት ሲሆን፣ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ዋነኛ ትግል የኢኮኖሚ ነጻነትን ማረጋገጥ ነው።
ታላቁ ፓን-አፍሪካኒስት ጁሊየስ ኔሬሬ እንዳስገነዘቡት፣ በመጀመሪያው የአፍሪካ ቅርምት ጎሳን ከጎሳ ያጋጨው የውጭ ኃይል፣ አሁን ደግሞ ሀገርን ከሀገር በማጋጨት አህጉሪቱን ደካማና የተከፋፈለች ለማድረግ ይጥራል። በእርግጥም በመከፋፈል ውስጥ የሚገኝ ክብርም ሆነ ታላቅነት የለም። ከተከፋፈልን ደካሞች እንሆናለን፤ ከተባበርን ግን በእኛ ላይ የሚመጡትን የጣልቃ ገብነት ኃይሎች አሳፍረን መመለስ እንችላለን።
በዚህ ታሪካዊ መጋጠሚያ ላይ፣ የኢትዮጵያ የመደመር ትውልድ ከራሱ አልፎ ቀጣናውን በፓን-አፍሪካዊ መንፈስ ለማስተሳሰር በጽናት ቆሟል። አፍሪካውያን የማይነጣጠሉ እና ዕጣ ፈንታቸው የተሣሠረ፣ የቀኝ ግዛት ድንበርን የሚሻገር የጠበቀ ወንድማማችነት ያላቸው ሕዝቦች ናቸው።
ለአብነት ያህል፣ ፉላኒ ጎሳ ከ19 በላይ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ሲገኝ፣ አካን በጋና እና አይቮሪኮስት፣ ኦሮሞ በኢትዮጵያ እና ኬንያ፣ አፋር በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ጅቡቲ፣ እንዲሁም ሶማሌ በቀጣናው የተለያዩ ሀገራት ተሰራጭቶ ይገኛል።
እ.አ.አ በ1902 በቅኝ ገዢዎች በተደረገ የድንበር ከለላ የበርታ ብሔረሰብ በሁለት ተከፍሎ በሱዳን እና በኢትዮጵያ እንዲኖር ተገዷል። ይህን ሐቅ ጠንቅቆ የተረዳው የመደመር ትውልድ፣ እነዚህን ሕዝቦች በፖለቲካ አጥር ማጠር እንደማይቻል በማመን፣ አፍሪካን እንደ አንድ ሕዝብ በማስተሣሠር የማበልጸግ ኃላፊነትን ወስዷል።
ኢትዮጵያ ይህንን የአብሮነት እና የመደመር እሳቤ በተግባር ለማሳየት የሰፋፊ መሠረተ ልማቶችን ትሥሥር እያከናወነች ትገኛለች። የአፍሪካ ኅብረትን አጀንዳ 2063 ለማሳካት እና ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውህደትን እውን ለማድረግ፣ ለጎረቤት ሀገራት ለምሳሌ ለጅቡቲ፣ ለሱዳን እና ለኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የምጣኔ ሀብት ትሥሥር እያፋጠነች ነው።
ከኬንያ ጋር የተዘረጋው የመንገድ መሠረተ ልማት፣ እንዲሁም በውኃ ተፋሰሶች ላይ የሚሠሩ ታላላቅ ግድቦች የዚሁ ታላቅ ፓን-አፍሪካዊ አሰባሳቢ ትሥሥር አካላት ናቸው።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባለፉት ሦስት ዐሥርት ዓመታት በሩዋንዳ፣ ላይቤሪያ፣ ሱዳን፣ ብሩንዲ እና ሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮውን በብቃት በመወጣት አህጉራዊ እና ቀጣናዊ መረጋጋትን አረጋግጧል። ይህም ኢትዮጵያ ለፓን-አፍሪካኒዝም ያላትን የተግባር ቁርጠኝነት ያረጋግጣል።
የ21ኛው ክፍለ ዘመን ፓን-አፍሪካኒዝም አፍሪካውያን በቅኝ ገዢዎች የተሰመሩላቸውን የፖለቲካ ድንበሮች በማንሣት፣ አህጉሪቱን ወደ አንድ የጋራ ነጻ ንግድ ቀጣና በማምራት የኢኮኖሚ ነጻነታቸውን የሚያረጋግጡበት ወሳኝ ምዕራፍ ነው።
የአፍሪካ ሕዝብ ብዛት ከ1.4 ቢሊዮን አልፎ ወደፊት በእጥፍ እንደሚያድግ ሲገመት፣ ይህ ታላቅ አምራች ኃይል እና ሰፊ ገበያ ትልቅ የመልማት አቅም ነው። በተጨማሪም አህጉሪቱ የተፈጥሮ ማዕድን፣ ነዳጅ፣ የውኃ ሀብት እና ሊታረስ የሚችል ሰፊ ለም መሬት፣ እንዲሁም የተለያዩ ማዕድናትን ጨምሮ የተትረፈረፈ ጸጋ ባለቤት ናት።
ከምዕራባውያን ገበያ ጥገኝነት ተላቅቀን ይህንን እምቅ ሀብት በማቀናጀት እና የምናመርተውን ምርት እርስ በርስ ብንለዋወጥ ታላቅ ስኬትን እንጎናጸፋለን።
ኢትዮጵያ ትናንት የፖለቲካ ነፃነት ዓርማ እንደነበረች ሁሉ፣ ዛሬ ደግሞ የመደመር ትውልድን በማስተባበር በቀጣናዊ ሰላም፣ በመሠረተ ልማት ዝርጋታ እና በአህጉራዊ ውህደት የላቀ ሚና በመጫወት ላይ ያለች ጽኑ ፓን-አፍሪካዊ ኃይል ናት።
አዲሱ ትውልድ አፍሪካውያን በመተባበር እና በወንድማማችነት ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ኅብረት እንዲፈጥሩ በጽናት የቆመ ኃይል ሆኖ ይቀጥላል፤ ምክንያቱም ለአፍሪካውያን ችግር ብቸኛው መፍትሔ ያለው በራሳቸው በአፍሪካውያን እጅ በመሆኑ ነው።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: