ኢትዮጵያ በታሪኳ ለነፃነቷ እና ለክብሯ የከፈለችው ዋጋ የተለየ ነው። የዚህ ታላቅ ድልና ፅናት ምስጢር ደግሞ በዘመናዊ መሣሪያ ብዛት ወይም በወታደር ቁጥር ብቻ የሚለካ ሳይሆን በኢትዮጵያዊው ወታደር "ልብ" ውስጥ ባለው ጥልቅ የሀገር ፍቅርና የማይበገር ጀግንነት ነው።
በቁርጥ ቀን ወደፊት የመግፋት እና ለሀገር ክብር የመሰዋት ባህል፣ የአርበኝነት ስሜት ከደሙ ጋር የተዋሃደው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዋና መለያ አሻራው ነው። ይህ "ከብረት የጠነከረ ልብ" በድንገት የተገኘ ሳይሆን፣ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ ክቡር የታሪክ እና የጀግንነት ውርስ ነው።
ከዓድዋ ተራሮች እስከ ካራማራ፣ ከሀገር ዳር ድንበር ጥበቃ እስከ ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች፤ የኢትዮጵያ ወታደር የሚታወቀው ባለው የህሊና ፅናት እና ፍጹም ታማኝነት ነው።
ውጊያ ላይ መሣሪያ ሊያልቅ፣ ስንቅም ሊጎድል ይችላል፤ የኢትዮጵያ ወታደር ልብ ግን በምንም ዓይነት ፈተና ውስጥ አይሸነፍም። በባዶ እግሩ የታገለበትን እና ሀገሩን ያስከበረበትን ታሪክ ስንመለከት፣ ድል የሚገኘው በወታደሩ ደረት ውስጥ ባለው እሳት እንጂ በብረት ጥንካሬ ብቻ አለመሆኑን በግልጽ ያረጋግጥልናል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ልብ የሚገለጸው በውጊያ ሜዳ ላይ በሚያሳየው ቆራጥነት ብቻ አይደለም። በሰላሙ ጊዜም ቢሆን ለሕዝብ ባለው ጥልቅ አክብሮት፣ ለሀገሩ ባለው ታማኝነት እና ለሰው ልጅ ባለው ሀዘኔታ ጭምር እንጂ።
በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በሶማሊያ፣ በቡሩንዲ እና በሱዳን የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የተሰማሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች የየአካባቢውን ሕዝብ እንደ ወንድም እና እህታቸው በመንከባከብ የዓለምን ሕዝብ ቀልብ ስበዋል። ይህ የሚያሳየው የወታደሩ ልብ የፅናት ብቻ ሳይሆን፣ የርኅራሄ እና የሰብዓዊነትም መኖሪያ መሆኑን ነው።
ዘመናት ሲቀያየሩ፣ ወታደራዊ ስልቶች እና የቴክኖሎጂ ደረጃዎች ሲሻሻሉ አሁንም ያልተቀየረው እና መቼም የማይቀየረው የኢትዮጵያ ወታደር የውስጥ ማንነት ነው።
ሀገርን የመጠበቅ አደራ ከወታደራዊ ግዴታ በላይ መንፈሳዊ እና ታሪካዊ ኃላፊነት እንደሆነ በጽኑ የሚረዳው ይህ ሠራዊት፣ ምንጊዜም የሀገራችን የፅናት አጥር እና የሰላሟ ዋስትና ሆኖ ይኖራል።
በእርግጥም የኢትዮጵያ ወታደር ያለው ዓይነት ልብ፣ የፅናት መንፈስ እና ለሀገር የመቆም ወኔ በየትኛውም የዓለም ማዕዘን በቀላሉ የሚገኝ አይደለም!
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: