130 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት፣ በኢኮኖሚ እና በሕዝብ ቁጥር የቀጣናው ግዙፍ የሆነችው ታሪካዊቷ ኢትዮጵያ በባሕር በር እጦት ብቻ ታንቃ እንድትቀጥል በዙሪያዋ የተዘረጋው ስውር የጂኦ-ፖለቲካ ድር እውነታው ምንድን ነው?
በአሁኑ ወቅት ግብፅ እና ሻዕቢያ ከሌሎች ኃይሎች ጋር በመሆን በአንድ አጀንዳ ላይ ስትራቴጂያዊ ውህደት ፈጥረዋል። ይኸውም ኢትዮጵያ በምንም ተዓምር ወደ ባሕር እንዳትደርስ ማድረግ የሚል ነው። ይህን አካሄድ ዓለም አቀፍ የደኅንነት ተንታኞች "የመዳረሻ መከልከያ ቀለበት" ብለው ይጠሩታል።
ለበርካታ ዓመታት የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ሲነሳ የሚታየው በኢኮኖሚ መነፅር ብቻ ነበር። ይህም ከፍተኛ የሎጂስቲክስ ወጪ፣ በየዓመቱ ለጅቡቲ ወደብ የሚከፈል በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እና የአንድ ወደብ ጥገኝነት ተደርጎ ይወሰዳል። በእርግጥ ይህ እውነት ቢሆንም፣ ሙሉ እውነታውን ግን አይገልጽም።
አሁን ላይ ሆነን ቀይ ባሕርን ስንመለከት ባሕሩ የንግድ መስመር ብቻ መሆኑ ቀርቶ የደኅንነት እና የህልውና ጉዳይ ሆኗል። የባሕረ ሰላጤው ሀገራት የገንዘብ ፉክክር፣ የሁቲ አማፂያን ድንገተኛ ጥቃቶች እና የታላላቅ ኃይሎች የጦር ሰፈሮች መገንባት ቀጣናውን ሙሉ በሙሉ የማይገመት አድርጎታል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በለንደኑ ቻተም ሃውስ ባደረጉት ንግግር፣ የኢትዮጵያን የባሕር በር ፍላጎት በልማት፣ በግንኙነት፣ በኃይል ደኅንነት እና በንግድ መነፅር በግልጽ አስረድተዋል። ይህ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት፣ ጉዳዩን እንደ ደኅንነት ስጋት ከመታየት አውጥቶ ቀጣናዊ ትስስር ለማምጣት ወደ ሚደረግ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት አሸጋግሮታል።
የኢትዮጵያ አቋም ግልጽ ነው። 130 ሚሊዮን ሕዝብ ይዞ፣ ቀጣናው በጦር መሣሪያ እና በፖለቲካ ቀውስ እየተናወጠ ባለበት ሁኔታ፣ ከባሕር በር ርቆ መኖር ራስን ለከፍተኛ አደጋ አጋልጦ መስጠት ነው የሚል ነው። ሆኖም ኢትዮጵያ የህልውና እና የልማት ጉዳይ ብላ የምታቀርበውን ይህን ጥያቄ፣ ጎረቤቶቿ ግን ከጥያቄው ጀርባ ሀገራችን ካርታ የመቀየር ፍላጎት እንዳላት አስመስለው እያቀረቡት ይገኛሉ። ይህ የተሳሳተ ትርጉም ነው እንግዲህ የግብፅን እና የሻዕቢያን አደገኛ የከበባ ቀለበት እየወለደ ያለው።
ሁሉም ኃይሎች የሚንቀሳቀሱት ከተለያየ የግል ጥቅም እና ፍላጎት ተነስተው ቢሆንም፣ የመጨረሻ ውጤታቸው ግን ኢትዮጵያን ማፈን ነው።
ለኢትዮጵያ ተፈጥሯዊው እና ቀራቢው የባሕር በር አሰብ ነው። ነገር ግን የአሥመራ መሪዎች ጂኦግራፊን ለመጠቀም የሚያስቡት ለቀጣናዊ ውህደት ሳይሆን ለሥልጣን ማቆያ እና በኢትዮጵያ ላይ የበላይነት ለማሳየት እንደ ስትራቴጂያዊ መሣሪያ አድርገው ነው። የባሕር በር ጥያቄ በተነሳ ቁጥር፣ በአሥመራ በኩል የንግድ እና የደኅንነት ጥያቄ መሆኑ ቀርቶ፣ የህልውና ዜሮ ድምር ፖለቲካ ሆኖ ይተረጎማል።
የካይሮ ስሌት ደግሞ በቆየው የሤራ ዲፕሎማሲ የታሸ ነው። ግብፅ የኢትዮጵያን ወደብ የማግኘት ፍላጎት በቀጥታ ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ እና ከዓባይ ውኃ ድርድር ጋር ታስተሳስረዋለች። ግብፅ የምትፈራው፣ ኢትዮጵያ የባሕር በር አግኝታ የኢኮኖሚ ነፃነቷ ሙሉ ከሆነ፣ በጎረቤት ሀገራት በኩል በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገው ዲፕሎማሲያዊ እና ወታደራዊ ጫና መላላቱ አይቀሬ መሆኑን ነው። ለካይሮ ... ዓባይ እና ቀይ ባሕር አንድ የጦር ግንባር ናቸው።
የሶማሊያ ውስጣዊ ድክመት፣ የሀገሪቱ የፌዴራል ክፍፍሎች እና የደኅንነት መዋቅሯ በውጭ ኃይሎች ላይ ጥገኛ መሆኑ፣ ለግብፅ ሤራ ምቹ አድርጎታል። የካይሮ ሰዎች ይህን ክፍተት በመጠቀም፣ ማናቸውንም የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የሉዓላዊነት ወረራ አስመስለው በመቀባት ሶማሊያን እንደ ምሽግ ለመጠቀም ይጥራሉ። በሌላ በኩል ሱዳን የገባችበት የእርስ በርስ ጦርነት፣ ሀገሪቱን የውጭ ስለላ ድርጅቶች መፈንጫ እና የደኅንነት ስጋቶች መናኸሪያ አድርጓታል።
የኤርትራ፣ የግብፅ እና የሱዳን ወታደራዊ መሪዎች በፈጠሩት ትስስር፣ የኢትዮጵያን ፍላጎት ለማደናቀፍ እና የውስጥ ታጣቂዎችን ለመደገፍ ይህን መሰሉን ቀውስ እንደ ምቹ አጋጣሚ ለመጠቀም ይሠራሉ። የኢትዮጵያ ጠላቶች የመከልከል ፖለቲካ ፍርሃትን እና የውስጥ አማፂያንን መደገፍን እንደ መሣሪያ ይጠቀማሉ። ኤርትራ ለግብጽ በመንበርከክ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ባንዳዎች እና ታጣቂ ኃይሎች ጋር ግንኙነት ፈጥራ የማወክ ፖሊሲዋን እየፈጸመች ነው።
የዚህ ዓላማው ኢትዮጵያ ሁልጊዜ በውስጥ ቀውስ ተጠምዳ ወደ ውጭ እንዳታይ ማድረግ ነው። ነገር ግን ይህ አካሄድ ቀጣናውን ወደ ባሰ ቀውስ ከመውሰድ ውጪ ለማንም አይበጅም። ሶማሊያ የሉዓላዊነት፣ ሱዳን ደግሞ የሰላም እና የልማት ጥያቄ አላቸው። ነገር ግን ግብፅ እና ኤርትራ ይህን የጎረቤቶቻቸውን ፍርሃት መሣሪያ በማድረግ ኢትዮጵያን ለማፈን ሲጠቀሙበት ነገሩ አደገኛ ይሆናል።
ኢትዮጵያ ይህን ቀለበት መስበር የምትችለው በሁለትዮሽ ድርድር ብቻ ሳይሆን፣ ሰፊና ቀጣናዊ የሆነ የጋራ የደኅንነት እና የንግድ ስምምነት በመፍጠር መሆኑን ታምናለች። ለዚህም ነው ለኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት ማለት ሌላውን መውረር ሳይሆን የቀጣናውን ልማት በጋራ ማፋጠን ነው የምንለው።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ፍትሐዊ፣ ሕጋዊ እና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ነው። ለዚህ ግልጽ የኢትዮጵያ ጥያቄ ደግሞ ፈረንሳይን ጨምሮ ሌሎች ኃያላን ሀገራት ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ አሳይተዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር አጀንዳ የአፍሪካ ቀንድን የኢኮኖሚ ዕድገት የማፋጠን፣ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል የመፍጠር እና የቀጣናውን ልማት ወደ አዲስ ምዕራፍ የማሸጋገር የጋራ ተጠቃሚነት መሻት ነው።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ሲኖራት ጎረቤቶቿ የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናሉ እንጂ አይጎዱም። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ግዙፍ የገበያ እና የማምረት አቅም ወደ ባሕር ሲፈስስ፣ በዙሪያዋ ያሉ ወደቦች በሙሉ የልማት እና የሀብት ማዕከል መሆናቸው አይቀሬ ነው።
ኢትዮጵያ ከፊቷ የተደቀነውን የከበባ ቀለበት ለመስበር ይህን የልማት እና የሰላም አማራጭ በተግባር ለዓለም በማሳየት ላይ ትገኛለች። ለዚህም ነው "ኢትዮጵያ የምትፈልገው ባሕርን እንጂ ጠላትነትን አይደለም!" የምንለው።
በንብረቴ ተሆነ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: