Search

የእሳት ልጅ እሳተ ነበልባል

እሑድ ሐምሌ 19, 2018 29

በኢትዮጵያውያን የዘመናት የትርክት ማህደር ውስጥ፣ ታላቅ ጀብዱ የፈፀሙ አባቶችንና ያንን አደራ መሸከም ያቃተውን ደካማ ተተኪ ለማነፃፀር “የእሳት ልጅ አመድ” የሚል ብሂል ይነገራል፡፡ ዛሬ ግን ይህ የሽንፈት ትርክት ተሰብሯል፡፡ ትናንት ቀይ ባሕርን በደማቸው የጠበቁት አባቶቻችን ‘እሳት’ ከነበሩ፣ የዛሬው ትውልድ ‘አመድ’ ሳይሆን፣ የታሪክ ስብራቱን የሚጠግን ‘እሳተ ነበልባል’ ሆኖ ተነስቷል፡፡

የኢትዮጵያ እና የቀይ ባሕር ቁርኝት የጂኦግራፊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የነፍስና የስጋ ትስስር ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ባሕሩን ከሩቅ የሚያዩ ጎብኝዎች ሳይሆኑ፣ በባሕሩ ዳርቻ የኖሩ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረታቸውን በውሃው ሞገድ ላይ ያዋቀሩ ታላላቅ ሕዝቦች ናቸው፡፡

“ፕላይኒ ትልቁ” እና “ፔሪፕለስ ኦፍ ዘ ኤሪትሪያን ሲ” በተሰኙት የጥንት የታሪክ መዛግብት እንደተረጋገጠው፣ አዱሊስ የዳማትና የአክሱም ነገሥታት ከሮምና ከግሪክ ጋር የሚገበያዩበት ታላቅ የባሕር በር ነበረች፡፡ ታላቁ አፄ ካሌብ እጅግ የዳበረ የባሕር ኃይል ገንብተው ቀይ ባሕርን በማቋረጥ የመንንና ደቡብ አረቢያን ይቆጣጠሩ እንደነበር የዘመኑ ፀሐፊ ኮስሞስ አስመስክሯል፡፡

የባሕርን ግዱን በማሳለጥ ረገድ ደግሞ የአፋርና የአርጎባ ሕዝቦች ያደረጉት አስተዋፅኦ ወደር የማይገኝለት የታሪካችን መሠረት ነው፡፡

እነዚያ “እሳት” የነበሩ አባቶቻችን ባሕሩን አሳልፈው ላለመስጠት የተዋደቁት ውድቀት የዘመናት ኩራታችን ነው፡፡ ጀግናው ራስ አሉላ አባነጋ በኅዳር ወር 1875 ዓ.ም በጉንደት ላይ መሽጎ የነበረውን የግብፅ ሰራዊት ዶግ አመድ አድርገውታል፡፡ በሽንፈታቸው የተንገበገቡት ግብፃውያን ከፍተኛ ጦር አሰልፈው በጉራዕ ምሽግ ሰርተው ቢመጡም፣ በጀግናው አሉላ ቆራጥነት ዳግመኛ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥተው ተመልሰዋል፡፡ ይህ ነው የእሳትነት ትርጉም! ባሕርን አለመንካት፣ ዳርቻን አለማስደፈር!

ሆኖም በዘመናት የፖለቲካ ሴራና ውጫዊ ጫና እንዲሁም በውስጣዊ ስህተቶች ምክንያት ኢትዮጵያ ከባሕር በሯ 60 ኪሎሜትር ርቃ እንድትገደብ ተደረገች፡፡ በዚህም የተነሳ አንዳንዶች ትውልዱን “አመድ” ሆኗል ብለው ፈርጀውት ነበር፡፡

ስለ ባሕር በር ማንሳት እንደ ወንጀል የተቆጠረበትና ልጆች ስለ መብታቸው ለማውራት የተሸማቀቁበት ጨለማ ዘመንም ነበር፡፡ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ አሳዛኝ ወደብ አልባ ሀገር ሆና ቆይታለች፡፡

ዛሬ ግን ዝምታው ተሰብሯል፡፡ እሳተ ነበልባል የሆነ አዲስ ትውልድ ተፈጥሯል፡፡ ይህ ትውልድ፣ የሰው ሀገር የሚዳፈር ተስፋፊ ሳይሆን፣ የራሱ የሆነውን የተፈጥሮ መብትና ሉዓላዊነት ዳግም የሚያስመልስ አሸናፊ ነው፡፡

ቀይ ባሕር ርካሽ ሸቀጥ ሳይሆን፣ የሉዓላዊነት ምልክት መሆኑን ይህ ትውልድ በሚገባ ተረድቷል፡፡ በርካታ ኃያላን ሀገራት ጥቅሙን አውቀው በዚሁ አካባቢ የጦር ሰፈሮቻቸውን ገንብተዋል፡፡ ይህ የኃያላን መሰባሰብና ወደ ባሕሩ እንዳንመለስ የሚደረግ የጠላቶች የቆየና ዛሬም የቀጠለ ሴራ የቀይ ባሕርን በር ለማስመለስ ለተነሳው ለዚህ እሳተ ነበልባል ትውልድ እንቅፋት ሊሆን አይችልም፡፡

ይህ የነቃ ትውልድ ባሕሩን አይሸጥም፤ የእሳት ልጅ እሳተ ነበልባል ነውና፣ ታሪካዊ መብቱን አረጋግጦ፣ የተቆረጠውን የደም ስር ቀጥሎ፣ የኢትዮጵያን አርማ ዳግም በቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ በክብር ያውለበልባል፡፡ ይህን ታላቅ ትውልድ ማንም ከደጃፉ አያስቀረውም! ማንም አያስቆመውም!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: